የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከ1 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አበረከተ

78

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከ1 ሺህ በላይ መጻሕፍትን ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዛሬ አበርክቷል።

'ሚሊዮን መጻሕፍት ለሚሊኒየሙ ትውልድ' በሚል መሪ ሀሳብ ለአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በሚከናወነው የመጻሕፍት ማሰባሰብ ንቅናቄ የተለያዩ ተቋማት ምላሽ እየሰጡ ነው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም ለመጀመሪያ ጊዜ ያሰባሰባቸውን ከ1 ሺህ በላይ መጻሕፍትን በዛሬው እለት አስረክቧል፡፡

መጻሕፍቱን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሲሳይ በቀለ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስረክበዋል፡፡

አቶ ሲሳይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት መጻሕፍቱ በመንገድ ዙሪያ ለሚደረጉ ምርምሮችና ትምህርታዊ ጉዳዮች የሚያግዝ ይዘት ያላቸው ናቸው።

በቀጣይም በመንገድ ዘርፍና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን በማሰባሰብ ለአብርሆት እንደሚያስረክቡ ጠቁመዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የመንገዶች አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን መጻሕፍት የማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

አብርሆት 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻሕፍትን የመያዝ አቅም እንዳለው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም