"የክፉዎች አፍራሽ ድርጊት ካሰብነው የብልጽግና ጉዞ አያግደንም" - ዶክተር ዓለሙ ስሜ

102

ሀዋሳ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ)የክፉዎች አፍራሽ ድርጊት ካሰብነው የብልጽግና ጉዞ አያግደንም ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ ፡፡

ነገ በሀዋሳ የሚጀመረው የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የመጀመሪያ ጉባኤ ተሳታፊዎች አሞራ ገደል ተብሎ በሚጠራው የሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ዓለሙ ስሜ "የክፉዎች አፍራሽ ድርጊት ካሰብነው የብልጽግና ጉዞ አያግደንም" ብለዋል።

ጠላቶች የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማደናቀፍ "ንፁሃንን በመግደልና እዚህም እዚያም እሳት በመለኮስ አገሪቱን ለመረበሽ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ" ያሉት ዶክተር ዓለሙ፤ "እነዚህ የክፋት ተልዕኮ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጊዜያዊ ፈተና ቢደቅኑ እንጂ ህልማቸው አይሳካም" ብለዋል።

"ችግኝ መትከል ለትውልድ የምትሻገርን ሀገር መገንባት ነው" ያሉት ሃላፊው፤ ብልፅግና ፓርቲም ከትናንት ትምህርት በመውሰድና ዛሬ ላይ ተግቶ በመስራት "የበለፀገችውን ኢትዮጵያ ለትውልድ ለማሻገር ተግቶ ይሰራል" ብለዋል፡፡

በመሆኑም የብልፅግና ግስጋሴያችንን ዕውን ለማድረግ "ደግ ደጉን ተክለን፣ ተንከባክበን እያሳደግን  ገዳዮችና ሌቦችን ነቅለን እያስወገድን እንቀጥላለን" ነው ያሉት።

ሴቶች የመውለድ፣ ተንከባክቦ የማሳደግና ሀገር የሚጠቅም ትውልድ የማፍራት "የእናትነት ፀጋ የተቸራቸው" እንደሆኑ የጠቀሱት ዶክተር ዓለሙ፤ በዚህ አብነት የሚተከሉትን ችግኞች በመንከባከብ ለትውልድ የሚሻገር በጎ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሠረት መስቀሌ በበኩላቸው ሊጉ ላለፉት ሶስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሥራዎችን በትኩረት ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በሴቶች ብቻ ከአራት ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን አስረድተዋል፡፡

የድህረ ተከላ እንክብካቤ ስራዎችንም በተደራጀ መንገድን እየመሩ መቆየታቸውን በማውሳት።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም በሴቶች አቅም ብቻ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከልና የእንክብካቤ ስራዎችን ለመስራት አቅደው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለምግብነት የሚውሉና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬና ሌሎች ችግኞች በስፋት እንደሚተከሉም ጠቁመዋል፡፡

"የከተማዋ አረንጓዴ፣ ውብና ፅዱነት በስተጀርባ የበርካታ ሴቶች አሻራ አለ" ያሉት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ናቸው።

እንደምንተክለው ችግኝ "ፍቅርን እየዘራን አብሮነታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል" ያሉት ከንቲባው፤ የከፋፋዮችን ሀሳብ ነቅሎ በመጣል አንድነቷ የፀናና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አመራሮችና የፓርቲው ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከየክልሉ የመጡ የሊጉ አመራርና አባላት ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም