በደቡብ የኦሞ ዞን ኦሞራቴ ኦሞ ድልድይ ኛንጋቶም ካንጋቴን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 69 በመቶ ደርሷል

151

ሰኔ 21 ቀን 2014(ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን እየተገነባ ያለው የኦሞራቴ ኦሞ ድልድይ ኛንጋቶም ካንጋቴን የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም 69 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ከዳሰነች ወረዳ ኦሞራቴ ከተማ ተነስቶ በኦሞ ድልድይ አልፎ በኛንጋቶም ወረዳ ካንጋቴን የሚደርስ 73 ነጥብ 84 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው።

መንገዱ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነባ ሲሆን በመንግሥት በተመደበለት 965 ሚሊየን ብር ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል።

የግንባታው ሥራ "ኤን ኬ ኤች" በተባለ ተቋራጭ የሚካሄድ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ሥራው ደግሞ በክላሲክ ኮንሰልቲንግ ኢንጂነሪንግ የግል ማህበር የሚከናወን ነው።በ2011 ዓ.ም ጥር የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ በ2014 ዓ.ም ጥር ወር መጨረሻ የማጠናቀቅ እቅድ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሊዘገይ ችሏል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ቃልኪዳን ቦጋለ፤ የመዘግየቱ ምክንያት ከቅርስ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ ክፍል ግማሹ በዩኔስኮ የተመዘገበ የአርኪዮሎጂ ቅርስ የሚገኝበት ሥፍራ በመሆኑ የተጽዕኖውን ሁኔታ ለማጥናት ሲባል መዘግየቱን ኢንጂነር ቃልኪዳን አስረድተዋል።

አሁን ላይ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙም 69 በመቶ ላይ ደርሷል ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሐንዲስ ኢንጂነር መስፍን ተህልቁ፤ በቅርስ ጥበቃ ምክንያት ግንባታው የዘገየ ቢሆንም ችግሩ ከተፈታ በኋላ በጥሩ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታው በተያዘለት በጀት በ2015 ዓ.ም ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ በተፋጠነ ሁኔታ በመከናወን ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

የሲሚንቶና የብረት አቅርቦት እጥረት በግንባታው ሂደት ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ችግሩ ከወዲሁ ሊፈታ እንደሚገባም አጽዕኖት ሰጥተውታል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የኛንጋቶም ወረዳ ነዋሪው አቶ ኩታይ ናኤላ እና የዳሰነች ኦሞራቴ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሄኖክ ግዛው፤ የመንገዱ መገንባት ከዚህ ቀደም ሕብረተሰቡ ሲያነሳቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅ የዳሰነች እና ኛንጋቶም ማኅበረሰብን የንግድና ማህበራዊ ግንኙነት በማሳለጥ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል ብለዋል።

በአካባቢው ያሉ አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች የአኗኗር ዘይቤያቸው እንዲቀየር ከማድረግ አኳያ እንዲሁም ለማህበራዊ አገልግሎቶች መፋጠን ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

አካባቢው ለኬንያ እና ደቡብ ሱዳን ቅርብ በመሆኑ ከአጎራባች አገሮች ጋር ለሚኖረው የንግድና ኢኮኖሚ ትስስርም ጠቀሜታ እንደሚኖረው ታምኖበታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም