የሀገርን አንድነትና ሠላምን ለማስከበር የድርሻችንን እንወጣለን- ወጣቶች

104

ነቀምቴ፣ ሻሸመኔ ፤ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ) አፍራሽ ቡድኖችን በመታገል የሀገርን አንድነትና ሠላምን ለማስከበር የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በነቀምቴ ከተማና ምዕራብ አርሲ ዞን ወጣቶች አስታወቁ።

“የዘመናችን የወጣቶች ድርሻ” በሚል  በነቀምቴ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ከተሳተፉት መካከል ወጣት ተስፋዬ ምትኩ እንዳለው፤ መንግሥት እየሰራ ባለው የሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ነው።

የአካባቢውንም ሆነ የሀገርን ሠላም በማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥም እንዲሁ።

ምክንያታዊ በመሆን በልማትና ሠላም ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደምታደርግም የገለጸችው ደግሞ ወጣት ሊዲያ ኢዶሳ ናት።

ወጣት ገላና ታመነ በበኩሉ፤  ሠላምና ልማትን  በማረጋገጡ ሂደት ውስጥ ወጣቶች ግንባር ቀደም በመሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል  ከመንግሥት ጋር  ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከር እንሚያስፈልግ ገልጿል።

አፍራሽ ቡድኖችን በመታገል የሀገርን አንድነትና ሠላምን ለማስከበር የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ወጣቶቹ ያስታወቁት።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ቶሌራ ረጋሣ ባስተላለፉት መልዕክት፤ወጣቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ በመሳተፍ የሥራ አጥነትን ችግር ለማቃለል አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የኑሮ ውድነትን በማቃለል ፣  በመልካም አስተዳደር ፣ በግብርና እንቅስቃሴ ውስጥ የወጣቱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን በማጠናከሩ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል ።

በተመሳሳይ የምዕራብ አርሲ ዞን ወጣቶች  በሻሸመኔ ከተማ በተወያዩበት  ወቅት  ከነገሌ አርሲ ወረዳ  የመጣው ወጣት እስማኤል  አሊ፤  የሸኔና መሰል የጥፋት ቡድኖችን በጥብቅ እንደሚቃወም ገልጿል።

ሰዎች  በማንነታቸው ምክንያት   ጥቃት  ሊፈፀምባቸው  ስለማይገባ  ይህ እንዲቆም  በፅናት  እንታገላለን ብሏል።

 ከኮፈሌ ወረዳ የመጣው ወጣት  ሀብታሙ ረጋሳ፤ ሰላምን ማስከበር የሁሉም  ድርሻ ቢሆንም የወጣቶች  ሚና የጎላ በመሆኑ በዚህ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

 በዞኑ በሄባን አርሲ እና ኮፈሌ ወረዳ   አዋሳኝ  ቀበሌዎች   አካባቢ  ከዚህ  በፊት  አሸባሪው ሸኔ  በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውሷል።

የአካባቢው ወጣቶች  ከፀጥታ አካላት ጋር  በመተባበር   ቡድኑን ከአካባቢው በማጽዳት  ሁሉም ሰው መደበኛ ስራውን ያለፀጥታ ችግር እያከናወነ ይገኛል ብሏል ወጣቱ።

“እኔም መንግስት የህግ   የበላይነትን  ለማስከበር   እየወሰደ  ያለውን  እርምጃ   በመደገፍ  አካባቢዬን ከመጠበቅ አልፎ መከላከያ  ሰራዊትን  ተቀላቅዬ   ለሀገሬ ዘብ  ለመቆም ፍቃደኛ እና ዝግጁ ነኝ” ሲልም አስታውቋል።

ውይይቱን የመሩት የምዕራብ አርሲ ዞን ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ  ወጣት ከማል አያኖ፣ በቅርቡ  አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ   በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመው ድርጊት በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የለውም ብሏል።

ወጣቶች ከእንደዚህ ዓይነት እኩይ ተግባር ራሳቸውን  በመቆጠብ  ዘላቂ ሰላም  እና ልማት ለማምጣት የራሳቸው ን ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል።

 በብልጽግና ፓርቲ  የምዕራብ አርሲ ዞን   ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ  መሀመድ  ሁሴን በበኩላቸው ፤  ወጣቶች  የሰላም ዋጋ ከፍተኛ  መሆኑን ተገንዝበው   ፀረ ሰላምና ፀንፈኞችን በመታገል የበኩላቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።