በወላይታ ዞን ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ

81

ሶዶ፣ ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን በዳሞት ወይዴ ወረዳ 73 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የበዴሳ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በዛሬው ዕለት ተመርቆ ለአገልግሎት በቃ።

ሆስፒታሉ ከ250 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን ከቻይና የመንገድ ስራ ፕሮጀክትና ከሌሎች የጤና ተቋማት ጋር በመተባበር የተገነባ መሆኑ ተነግሯል።

በሆስፒታሉ ምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ፤ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መንግስት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከእነዚህ አንዱ የጤና ተቋማት ግንባታ በፍትሃዊነት ተደራሽ ማድረግ ሲሆን ዛሬ የተገነባው የበዴሳ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልም የዚህ ዝራ ማሳያ ነው ብለዋል።

በክልሉ 43 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ኃላፊው የጤና ዘርፉን ሽፋን ከፍ ለማድረግ ከጤና ኬላ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን የመደገፍ ስራ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰመስተዳድርና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት በጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ የህዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የጤና ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሙያዊ ስልጠናና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ እርስበርስ ከመደጋገፍ አኳያ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በከተማው አንድ ጤና ጣቢያ ብቻ የነበረ በመሆኑ በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ሲነሳ የነበረውን ጥያቄ ለመመለስ በተደረገው ጥረት አጋር አካላት በማስተባበር ግንባታው በአጠረ ጊዜ እንድመለስ መደረጉን ጠቁመዋል።

ሆስፒታሉን ግንባታና ለአገልግሎት የሚያበቁ የተለያዩ ግብአቶች ግዠ ጨምሮ ከመንግስትና ከተለያዩ አጋር አካላት ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ እንደፈጀ ገልጸው ከ250 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ