በአሜሪካ የሚኖር የ9 ዓመት ታዳጊ ለአብርሆት ከ100 በላይ መጻሕፍትና 1 ሺህ ዶላር አበረከተ

103

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ ነዋሪ የሆነው ዳንኤል አዲሱ የተባለ የ9 ዓመት ታዳጊ ለአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ከ100 በላይ መጻሕፍትና 1 ሺህ ዶላር አበረከተ።

በአሜሪካ፣ ካሊፎኒያ የሚኖረው ታዳጊው ከወላጅ እናቱ ጋር ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በዛሬው እለት መጻሕፍቱን ለአብርሆት አስረክቧል።

የታዳጊው ወላጅ እናት ወይዘሮ አትጠገብ ግርማ፤ ዳንኤል በራሱ ተነሳሽነት መጽሐፍቱን ለአብርሆት ለማበርከት መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም በዛሬው እለት 100 መጽሐፍት፣ ሁለት ላፕቶፖች እና 1 ሺህ ዶላር ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

የዳንኤልን አርአያ በመከተል በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ታዳጊዎች በአገራቸው እየተከናወነ ላለው በጎ ተግባር ተሳታፊ በመሆን አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጠይቀዋል።

መጻሕፍቱን የተረከቡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የታዳጊውን ተግባር አድንቀው ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ታላቅ አበርክቶ መሆኑን ገልጸዋል።

ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ሁለገቡ የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ከታህሳስ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን የመጻህፍት የማሰባሰብ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ቤተ-መጽሐፍቱ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን መጻህፍት የመያዝ አቅም አለው።