የድህነት ትግሉን ለማሸነፍ ተፈጥሮን መጠበቅ ወሳኝ ነው -አቶ ኡስማን ሱሩር

192

ሶዶ፣ ሰኔ 21/2014 (ኢዜአ) የተፈጥሮን ሀብት በአግባቡ በጠበቅና መጠቀም ድህነትን ማሸነፍና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር አስገነዘቡ።

በወላይታ ዞን የ2014 የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር "አረንጓዴ አሻራ ልማት ለትውልዳችን" በሚል መሪ ቃል በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የሾላ ኮዶ ቀበሌ በይፋ  ዛሬ ተጀምሯል ።

በዞኑ በሁሉም አከባቢዎች ለተከታታይ 30 ቀናት የሚቆይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ  የክልል፣ የዞንና የአከባቢው ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።

መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር "በየአካባቢያችን ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በመጠበቅና በመጠቀም ድህነትን ማሸነፍና ኢኮኖሚያዊ እድገታችንን ከፍ ልናደርግ ይገባል"።

ካሁን በፊት ድህነትና መሠል ችግሮችን ለመቅረፍ በርካታ የግብርና ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ብቻውን የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉን ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ታምኖበት ወደተግባር በመገባቱ ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

"የኢኮኖሚ መሠረቱ ግብርና መሆኑን ተከትሎ የተፈጥሮን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ድህነትን ማሸነፍና  ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል።

በአረንጓዴ አሻራው ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን መተካት የሚያስችሉ ችግኞች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፍራፍሬ ምርቶችና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች በተለይ የኑሮ ውድነቱን ከመቋቋም አኳያ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አቶ ኡስማን አመልክተዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት እንደ ክልል ከ18 ቢሊዮን በላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የተተከሉ መሆኑን ጠቅሰው ለምግብነት፣ ለውሃና አፈር ጥበቃ እንዲሁም ለደን ሽፋን ምጣኔ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግኞችን ሲተክል የሚያስገኛቸውን ጠቀሜታዎች በአግባቡ በመረዳትና በመንከባከብ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማ በበኩላቸው በዞኑ 96 ሚሊዮን ችግኞች በማፍላት 63 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መትከል መጀመሩን ጠቁመዋል።

የተዘጋጁት ችግኞች ለምግብነት፣ ለእንስሳት መኖነት፣ ለጥላ እንዲሁም ለአፈርና ውሀ ጥበቃ ጠቀሜታ የሚውሉ ዛፎችን ያካተቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"አረንጓዴ አሻራ ከመርሃግብር ያለፈ ጉዳይ ነው" ያሉት አቶ አክሊሉ በምግብ ራስን የመቻል ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት ከ360 በላይ የንዑስ ተፋሰሶች ላይ የተተከሉ ችግኞች ከ84 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን አመልክተው በቀጣይም ለሚተከሉ ችግኞች እንክብካቤና ጥበቃ የተሻለ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሶዶ ዙሪያ ወረዳ የሾላ ኮዶ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙንኤ ባሳ ባለፉት ሶስት ዓመታት በማሳቸው ከ145 ችግኞች በላይ መትከላቸውን ተናግረዋል።

ዘንድሮ የዝናብ ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ 50 ችግኞች ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቅሰው በዛሬው ዕለትም 15 ችግኞች መትከላቸውን ገልጸዋል።

በባለፉት ዙሮች ለተከሏቸው ችግኞች በቂ ክትትልና እንክብካቤ በማድረጋቸው አብዛኛዎቹ መፅደቃቸውን አክለዋል።

በዚህም የቡና ማሳቸውን ለመጠበቅና ለጥላነት የሚውሉ የወይራና የቀርከሃ  ችግኞች መትከላቸውን ጠቅሰዋል።

ሌላኛዋ የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ሾንጊቴ ባዛ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተለይ የአቮካዶ  ችግኝ በብዛት እንደሚተክሉና በዚህም ከራሳቸው አልፎ የሌሎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም