በቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል 58 ዓይነት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ አድርጓል

85

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል 58 ዓይነት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ምርታማነት በእጥፍ እንዲጨምር ማስቻሉን ገለጸ፡፡

በምርምር እየቀረበ ባለው ምርጥ ዘር በተጨባጭ ምርታማነት እየጨመረ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ተናግረዋል።

በግብርና ምርምር ማዕከሉ የብሔራዊ የጤፍ ምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ወርቁ ከበደ፤ እስካሁን 58 ዓይነት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመትም ሁለት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን ተደራሽ ማድረጉን ጠቅሰው፤ የጤፍ ምርታማነት እንዲጨምር የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል ብለዋል።

ዘሩን በማዳቀል እና በቤተ-ሙከራ የሚፈለገው ንጥረ ነገር እንዲኖሩት በኬሚካል በማድረቅ የዘር ማሻሻያ ምርምር እየተሰራ ስለመሆኑም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በማዕከሉ የሚወጡ የምርምር ውጤቶች በቂ ዝናብ ለሚያገኙ፣ ዝናብ አጠር ለሆኑ እንዲሁም ለደጋ አካባቢዎች የሚስማሙ የጤፍ ዝርያዎችን ማቅረብ መቻሉን አስረድተዋል።

የዝናብ እጥረት ለሌለባቸው አካባቢዎች ብቻ የሚሰማሙ 38 የጤፍ ዝርያዎች ለአርሶ አደሮች መሰራጨታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በተሰራው የምርምር ሥራ የጤፍ ምርታማነት መጨመሩን ጠቅሰው፤ በዚህም በ1 ሄክታር መሬት 8 ኩንታል ይገኝ የነበረውን ምርት ከ18 እስከ 20 ኩንታል ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የጤፍ ዝርያን ዘርተው በማባዛት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የሚያደርጉ የግል እና የመንግሥት ድርጅቶችም ከ1 ሄክታር ከ25 እስከ 30 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገር ደረጃ የጤፍ ምርት የሚዘራበት የማሳ ስፋት ድሮ ከነበረው 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ማለቱንም ገልጸዋል፡፡

በአገር ደረጃ በዓመት ይገኝ የነበረው ምርትም ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ከፍ ብሎ በአሁኑ ወቅት ወደ ከ6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ በጤፍ ዘር ብዜት የተሰማሩት አቶ አመሃ አብርሃም፤ ላለፉት አምስት ዓመታት በማዕከሉ የተሻሻሉ የጤፍ ዘርያዎችን እያባዙ ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከስምንት በላይ የተለያዩ የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን በማባዛት በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች እያሰራጩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም አርሶ አደሮች በራሳቸው የዘር ብዜት ሥራ እንዲሰሩ የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችን መዝራት ከጀመሩ ወዲህ ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

የግብርና ምርምር ማዕከሉ ከሚያከፋፍለው የጤፍ ዝርያዎች ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ቢሾፍቱ የሚገኘው የግብርና ምርምር ማዕከል ከጤፍ ምርት በተጨማሪ አገር አቀፍ የዱረም ስንዴ አስተባባሪ በመሆንም የምርምር ሥራውን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡