የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አመራርና ሰራተኞች ደም ለገሱ

 አዲስ አበባ  ሰኔ 21/2014 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አመራርና ሰራተኞች የደም ልገሳ አደረጉ፡፡

በመስቀል አደባባይ በዛሬው እለት በተካሄደው መርሃ ግብር ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ደም መለገሳቸው ተገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፤ የባለስልጣኑ ስራተኞች የደንብ ጥሰትን ከመከላከል በተጓዳኝ በክረምቱ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ለመሳተፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በመስቀል አደባባይ በዛሬው እለት የተካሄደው የደም ልገሳም የዚሁ ተግባር አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም በችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን በማደስና ለአብርሆት ቤተ መጽሀፍት የመጽሃፍ ልገሳ በማድረግ ክረምቱን በበጎ ተግባር ለማሳለፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች የትምህርትና ቅስቀሳ ባለሙያ አቶ ንጋቱ አለምአንተ፤ የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን አመራርና ሰራተኞች ላደረጉት መልካም ተግባር አመስግነዋል።

በክረምቱ በተለይም ተማሪዎች፣ የተቋማት ሰራተኞችና ሌሎችም የማህበረሰብ ክፍሎች ደማቸውን በመለገስ ደም የሚሹ ዜጎችን ህይወት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም