ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ያለመ የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ እየተካሄደ ነው

107

ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥና የማኅበረሰብን አብሮነት ለማጠናከር ያለመ የምክክር መድረክ በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከስተርሊንግ ፋውንዴሽን ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ “የማኅበረሰብን ሰላምና አብሮነት ለማጠናከር የሃይማኖቶች የጋራ ዕሴቶች ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ  እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ አቶ ደሳለኝ አስራደ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ፣ አምባሳደር እሸቱ ደሴ የሠላም ሚኒስትር አማካሪ፣ አቶ ዘውዱ ማለደ የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እንዲሁም ከ300 በላይ የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት የሃይማኖት ተቋማት ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መድረኩ በጎንደርና አካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ነው።

በመድረኩ ሰላምን በመገንባት ጉልህ ድርሻ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ማለትም የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች እየተሳተፉ ይገኛል ብለዋል።

በሰላም ግንባታ ረገድ የሃይማኖት አባቶችና የማህበረሰቡን ሚና የተመለከቱ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚካሄድባቸው አንስተዋል።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ያስረዱት ቀሲስ ታጋይ፤ በመድረኩ መጠናቀቂያ ላይ ከጸጥታ አካላት፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከማህበረሰቡ የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ስራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤