በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የገላና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

103

ነጌሌ፣ ሰኔ 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ቶሬ ከተማ በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የገላና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የወረዳው አስተዳደር ገለጸ።

ሆስፒታሉ የነዋሪዎችን የአመታት ጥያቄ የመለሰ መሆኑን የገለጹት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ዴንባ፤ “ሆስፒታሉ ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የማድረግ አቅም አለው” ብለዋል፡፡

የሆስፒታሉን የግንባታ ወጪ የክልሉ መንግስት እንደሆነም ተናግረው፤ የለውጡ መንግስት የጀመረውን በመጨረስ ለህዝብ የገባውን ቃል እንደሚያከብር የታየበት ግንባታ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ በዳሳ ጂሎ በበኩላቸው የሆስፒታሉ የውስጥ አደረጃጀት የክልሉ ጤና ቢሮ በመደበው 15 ሚሊዮን ብር እንዲሟላ መደረጉን ገልጸው፤ ከክልሉ መንግስት አንድ ዘመናዊ አምቡላስም ተመድቦለታል ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ በሙሉ አቅም አገልግሎት እንዲሰጥ ውሀ፣ ጀኔሬተርና የከፍተኛ ቀዶ ጥገና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች እንዲሟሉ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ቀርቧል ብለዋል፡፡

የቶሬ ከተማ ነዋሪዎች የሆስፒታሉን ስራ መጀመር አስመልክቶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ ጥያቄያቸውን እንደመለሰ ተናግረዋል።

ህሙማን ለተሻለ ህክምና ረጅም ርቀት ከመጓዝ እንደሚድኑም ገልጸዋል።

የተጀመሩ ሌሎች የመሰረተ ልማት ተቋማት በጊዜ እንዲጠናቀቁ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር የሚያደርጉ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤