ምክር ቤቱ በላይኛው ጉደር ግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ላይ የታዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ

147

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በላይኛው ጉደር ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት የታዩ የኦዲት ግኝቶችን እስከ ሐምሌ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የማስተካከያ እርምጃ ወስዶ እንዲያቀርብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የመስኖናና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ያቀረበውን የላይኛው ጉደር ግድብና መስኖ ልማት ፕሮጀክት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ዛሬ ግምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴው በፕሮጀክቱ የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ሚኒስቴሩ የሰጠው ምላሽና ማብራሪያ በቂ ነው ብሎ እንደማያምንና ዋና ኦዲተር ልዩ ኦዲት አድርጎ እንዲያቀርብም ጠይቋል።   

ሚኒስቴሩ የግንባታ ስራው ከመጀመሩ በፊት የመሬት ይለቀቅልኝ ጥያቄ ማቅረብ ሲገባው አለማቅረቡ በኦዲት መረጋገጡን ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል።

በቅድመ ብቃት ጨረታ ውድድር አልፈው የሚመጡ ተጫራቾች ውል በሚዋዋሉበት ጊዜ አስተማማኝ የብቃት ደረጃ ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የድህረ ብቃት ግምገማ ያልተደረገ  መሆኑንም እንዲሁ።

በአዋጭነት ጥናቱ መሰረት ከ16 ሺህ በላይ ሰዎች ካሳ  ለመክፈል የተገመተው ከ571 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሆንም እስካሁን ለ136 ሰዎች ብቻ ከ278 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መፈጸሙ ተነስቷል።

በአዋጭነት ጥናቱ ከተገመተው ገንዘብ 48 በመቶው ለካሳ ክፍያ ጥቅም ላይ ቢውልም 99 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ግን ካሳ አልተከፈላቸውም ነው የተባለው።

ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ወደስራ አለመግባቱንና አሁን ባለበት አፈፃፀም ከተያዘለት ጊዜ አንፃር ዝቅተኛ መሆኑም ተመላክቷል።

በፕሮጀክቱ ኦዲት ግኝት መሰረት ሚኒስቴሩ ያደረገውን ማሻሻያ አስመልክቶ ለቋሚ ኮሚቴው የሰጠው ምላሽና ማብራሪያ በቂ እንዳልሆነ ተገልጿል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክርስትያን ታደለ ሚኒስቴሩ የኦዲት ግኝት ማስተካከያውን ለቋሚ ኮሚቴው እስከ ሐምሌ 5ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

ፕሮጀክቱን ለብልሹ አሰራር የሚዳርጉ ጉዳዮችን ለይቶ የታዩ ክፍተቶችን በመሙላትና ጥፋተኛ የሆኑ አካላት ላይ እርምጃ ወስዶ በሁለት ወራት ጊዜ እንዲያሳውቅም ጠይቀዋል።

ሚኒስቴሩ የሚያካሂዳቸው የልማት ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት የተሰራላቸው፣ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የተደረገባቸውና የማህበረሰቡን ተጠቃሚነትና ባለቤትነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን መርህ አድርጎ ሊንቀሳቀስ ይገባልም ብለዋል።   

ከላይኛው ጉደር ፕሮጀክት ጋር ተያያዥ የሆኑ የኦዲት ግኝት ማስተካከያ ሪፖርት በየሶስት ወሩ እንዲያቀርብም ታዟል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በመሬት ዝግጅት፣ አብሮ በመስራት፣ በዲዛይንና ካሳ ክፍያ መሰራት የነበረባቸው ባለመከናወናቸው ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዳይከናወን አድርጓል ብለዋል።   

ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዘ ችግር በመኖሩ ልዩ ኦዲት እንደሚደረግም አመላክተዋል።  

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚንስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው ተቋሙ አዲስ እየተዋቀረ መሆኑንና አመራሩም በቅርቡ የመጣ መሆኑን እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል።

በቀጣይም  ከፕሮጀክቱ ጋር የተያየዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ስራ መጀመሩን አብራርተዋል።

በላይኛው ጉደርና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በአሰራር የተደገፉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

በቋሚ ኮሚቴውና በዋና ኦዲተር የተሰጡ አቅጣጫዎችን በእቅድ በማካተት እንደሚሰራም ተናግረዋል።