የሱዳን ሃይል ኢትዮጵያን ለመክሰስ የሚያደርገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም

180

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የገባው የሱዳን ሃይል ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ለመክሰስ የሚያደርገው ሙከራ ተቀባይነት የለውም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ መንግስት ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮ-ሱዳን አዋሳኝ አካባቢ ወደ በኢትዮጵያ ዘልቆ በገባ የሱዳን መደበኛ ወታደራዊ ሃይል ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።

ጉዳቱ የደረሰው በሱዳን መደበኛ ሃይል ላይ እና በአካባቢው ሚሊሻ ላይ እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫ፤ የሱዳን መደበኛ ሰራዊት በአሸባሪው የህወሃት ሃይል የሚደገፍ መሆኑንም ጠቁሟል።

በደረሰው ጉዳት ማዘኑን ገልጾ፤ ስለሁኔታው በቅርቡ ምርመራ እንደሚካሄድ አመልክቷል።

ይህ ሆኖ ሳለ በድንበር አካባቢ ያልተገባ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የሱዳን መከላከያ ሃይል ኢትዮጵያን ለመወንጀል የሚያደርገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ የገባው የሱዳን ሃይል ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ለመክሰስ የሚያደርገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል።

የሱዳን መንግስት ሁኔታው ወደከፋ ግጭት እንዳያመራ ጥረት እንደሚያደርግ ተስፋ ያለው መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት ገልጿል።

ድርጊቱ ረጅም ጊዜ የዘለቀውን የኢትዮጵያና የሱዳንን ግንኙነት አደጋ ላይ ለመጣል ሆን ተብሎ የሚፈጸም እንደሆነ እምነቱን የገለጸው መንግስት፤ ድርጊቱ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያን የሰላምና ልማት ጉዞ ለማደናቀፍ የሚደረግ ጥረት እንደሆነ አመልክቷል።

ችግሩን ለማባባስ ጥረት ቢደረግም ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኗን መግለጫው አረጋግጧል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤