የ2015 ረቂቅ በጀት ቁልፍ የሪፎርም ስራዎችን በማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት አድርጓል

132

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የ2015 ረቂቅ በጀት ቁልፍ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ላይ ትኩረት ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለጸ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2015 ረቂቅ በጀት ላይ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ አካሂዷል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ በወቅቱ የረቂቅ በጀቱ ዝግጅት ታሳቢ ያደረጋቸውና ዋና ዋና ትኩረቶችን አብራርተዋል።

በጀቱ አጠቃላይ የገቢ አሰባሰብ አቅምንና የአገርንና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጀመሩ የታክስ ማሻሻያ ስራዎች በማዘመን ከ400 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታሳቢ መደረጉን ተናግረው፤ ተጀምረው ላልተጠናቀቁ ለዋና ዋና መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እና ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በዚህም ቁልፍ የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሳይስተጓጎሉ ማጠናቀቅን መንግስት በአቅጣጫ መያዙን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች የቀረበውን የበጀት ገለጻ መሰረት በማድረግ የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት፣ የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ በጦርነትና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመገንባት፣ በጀትን ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ ከመጠቀም አኳያ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ የ2015 ረቂቅ በጀት ለቁጠባና ለውጤታማ የበጀት አጠቃቀም ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

ዶክተር እዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የገቢ አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የተጀመሩ የፖሊሲና አዋጅ ማሻሻያ ስራዎችን የማጠናከር ተግባር እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዚህም ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል።

የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸው፤ በጦርነት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን በዘላቂነት ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል፡፡

የ2015 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት 786 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ሆኖ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ረቂቅ በጀቱ በተለያዩ መድረኮች የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓትነት በመውሰድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤