የሀዋሳ ከተማ የፓርክ ልማትና የመግቢያ በር ፕሮጀክት ግንባታ ተጀመረ

ሀዋሳ ሰኔ 20/2014 (ኢዜአ) የሲዳማን ባህልና ትውፊት ለማስተዋወቅና ለሀዋሳ ከተማ ልዩ ድምቀት ይሆናል ተብሎ የታለመለት የፓርክ ልማትና የመግቢያ በር ፕሮጀክት ግንባታ ስራ በይፋ ተጀመረ፡፡

በጥቁር ውሀ በኩል ባለው የሀዋሳ መግቢያ በር ላይ የሚገነባው ፕሮጀክት ይፋዊ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል ፡፡

ለፕሮጅክቱ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙ ተጠቁሟል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከተማዋ በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ግንባር ቀደም ተወዳዳሪ ሆና እንድትቀጥል ከማድረግ ባለፈ በውበት፣ በጽዳት፣ በቱሪዝም፣ በኢንቨስትመንና በህብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራዎቿ የብልፅግና ተምሳሌት ሆኗ እንድትቀጥል እየተሰራ ነው ፡፡

ዛሬ በይፋ ሥራው የተጀመረውን ፕሮጀክት ጨምሮ በአሁን ወቅት የታቦር ተራራ ልማት፣ የውስጥ ለውሰጥ አስፋልቶች እንዲሁም የመንገድ ዳር መብራትና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ እንደሆነ ከንቲባው ጠቁመዋል ፡፡

የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት የመግቢያ በር ፕሮጀክቱ ዲዛይን የሲዳማ ህዝብን ባህልና ትውፊት በሚገባ የሚገልፁ የኪነ ሕንፃ ሥራዎች የተካተቱበት እንደሆነ የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ሀዋሳ የፍቅር፣ የአንድነትና አብሮነት ከተማ መሆኗን በጉልህ የሚያሳይ ነው ብለዋል ፡፡

ፕሮጀክቱ ከሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ጋር የሚሳለጥና የሀዋሳን ማራኪነት የሚያጎላ እንደሆነም ጠቁመዋል ፡፡

በአሁን ወቅት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ ከተማዋን የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ገፅታ እንደሚያላብሷት ነው አክለው የተናገሩት ፡፡

የዲዛይን ሥራውን ያከናወነውና ፕሮጀክቱን በሀላፊነት የሚመራው የቢርናድ ዲዛይንና አማካሪ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፀጋዬ ተክሉ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ 100 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ እንደሆነ ገልፀው "የጥራት ደረጃውን እንደጠበቀ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ቀደም ብሎ እንዲጠናቀቅ ጥረት እናደርጋለን" ብለዋል ፡፡

"የቱሪስት ከተሞችን የማህበረሰቡን ባህልና ታሪክ በሚገልፁ ኪነ ሕንፃዎች ማስዋብ ባደጉት ሀገራት የተለመደ ነው" ያሉት ኢንጂነር ፀጋዬ በዚህ ረገድ ፕሮጀክቱ ሀዋሳን ከኢትዮጵያ ከተሞች ቀዳሚ እንደሚያደርጋት አመላክተዋል።

የኢትዮጵዊያን ቀደምት ኪነ ሕንፃ ጥበባት ዳግም እንዲያብቡ መነሻ ሊሆን የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል ፡፡

መግቢያ በሩ ዘመናዊ የካሜራ ሥርአት እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት መረጃ መሰብሰቢያና ማደራጃ ቋት ያለው እንደሆነ ገልፀው ለጥናትና ምርምር ሥራዎች አጅግ አጋዥ እንደሆነ ጠቁመዋል ፡፡

ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ በተለይ በውስጡ ያካተታቸው የቅርፃ ቅርፅ ፣ የባህል አልባሳትና ቁሳቁስ እንዲሁም የግብርና ውጤቶችና የሌሎች ምርቶች መሸጫ ሱቆች ቋሚ የሥራ ዕድል የሚከፍቱ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ፡፡

በፕሮጀክቱ ግንባታ ማስጀመሪያ  ስነ ስርአት ላይ ከንቲባውን ጨምሮ የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ፣ ባለድርሻ አካላት፣ የባህል አባቶች እንዲሁም  ተገኝተዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም