የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ከሁለት የመምህራን ኮሌጆች ጋር የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ከሁለት የመምህራን ኮሌጆች ጋር የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ከደብረ ብርሃንና አሰላ መምህራን ኮሌጆች ጋር የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት እና የደብረ-ብርሃንና አሰላ መምህራን ኮሌጅ ተወካዮች ተፈራርመዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረትም ከመጪው ሃምሌ 1 ጀምሮ 4ሺ እጩ መምህራን በክረምት እንዲሁም በቅዳሜና እሁድ የትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ይሆናል ተብሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ዘላለም ሙላት በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የመምህራንን አቅም በማሳደግ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በተለይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት የልጆች መጻኢ እድል የሚወሰንበትና መሰረት የሚጣልበት በመሆኑ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡
"መሰረቱ ያማረ፤ መጨረሻው ያምራል" ያሉት ሃላፊው ህጻናት እንዲበቁ እና እንዲነቁ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስምምነቱ 4ሺ መምህራን ከሰርትፊኬት ወደ ዲፕሎማ ደረጃቸው ከፍ እንዲያደርጉ ያግዛልም ብለዋል፡፡
የደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር መባ ፈጠነ፤ ኮሌጁ ከዚህ በፊት በቅድመ አንደኛ ደረጃ በሁለት ዙር በርካታ እጩ መምህራንን በማሰልጠን ማስመረቁን ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በተስማሙት መሰረትም ከሀምሌ ጀምሮ 2ሺ 500 መምህራንን በክረምትና በቅዳሜና እሁድ መርሃ ግብር ለማሰልጠን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የአሰላ መምህራን ኮሌጅ ተወካይ ረዳት ፕሮፌሰር ጎሳ ግርማ በበኩላቸው፣ የመምህራንን አቅም መጎልበት የመጪዎቹ አገር ተረካቢ ህጻናትን ተስፋ ማለምለም ነው ብለዋል፡፡
ኮሌጃቸውም ለመጀመሪያ ጊዜ 1ሺ 500 መምህራንን ለማሰልጠን ውል መውሰዱን ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ዕድል ያገኙ መምህራንም ባገኙት እድል መደሰታቸውን ገልጸው ከስልጠናው በኋላም ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት መርሃ ግብር ከዚህ በፊት በሰርትፊኬት በተመረቁ መምህራን ይሰጥ እንደነበር ተመልክቷል፡፡