በክልሉ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሳተፋሉ - ፌዴሬሽኑ

72

ሀዋሳ ሰኔ 20/2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወቅት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የክልሉ የወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

 ወጣቶቹ በተሳትፏቸው ከ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር በላይ ሀብት የሚገመት የልማት ስራ እንደሚያከናውኑም ተመላክቷል።

የክልሉ ወጣቶች ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት ሱልጣን ዓሊ በዘንድሮ የ2014 ዓ.ም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ወጣቶች በልዩ ልዩ የስራ መስኮች እንዲሳተፉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተሰርተዋል።

በዚህም ከ5 ሚሊየን 590 ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቧልም ብሏል።

በዚህም ከመንግስትና ከህዝብ ሊወጣ የሚችልን ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት የሚገመት ስራ እንደሚሰራም ነው የገለጸው።

ወጣቶቹ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በማቀናጀት የመንግስትን ወጪ ከመታደግ ባለፈ ለህዝብ ጥያቄዎች በጋራ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩ ነው የገለጸው።

ከበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም ልዩ ልዩ ስራዎችን የማከናወን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ለዚህም ከክልል መዋቅር እስከ ቀበሌ ድረስ የሚገኙ የወጣቶች መዋቅሮች ከሌሎች አደረጃጀቶች ጋር ከዕቅድ ጀምሮ ለተግባር አፈጻጸም በተቀናጀ መልኩ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል።

የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ፣ የአረጋውያን ቤት ግንባታና ጥገና እንዲሁም በሌሎች በተለዩ በ13 የትኩረት መስኮች  ወጣቶቹ ከሚሳተፉባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መሆናቸው ተጠቅሷል።

በየዓመቱ በተሳትፎም ሆነ በውጤታማነት ከፍ እያለ የመጣው የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚፈጥረው ማህበራዊ መስተጋብርና መልካምነት ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።

ይህንንም በመረዳት የክልሉ ወጣቶች ካለፉት ዓመታት በበለጠ በከፍተኛ ሁኔታ እንድሳተፉ እና በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ እንድያደርጉ ጥሪ አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም