አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢኮኖሚ መስክ የነበሩ ስብራቶችን መቅረፍ ያስቻለ ነው-የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

138

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ)  አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ አፈጻጸምን ጨምሮ በኢኮኖሚ መስክ የነበሩ ስብራቶችን መቅረፍ ያስቻለ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡

በቀጣይ በተለይ በግብርናው መስክ ምርትና ምርታማነትን በማሻሻል የኑሮ ውድነትን ጫና ለማቃለል የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ በሀገራዊ የሰላምና ደህንነት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ የተለያዩ አቅጣጫዎችን በማሳለፍ  አጠናቋል፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዳሉት፤ ፓርቲው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከርና ፈተናዎችን ደግሞ ተባብሮ በመፍታት ለመሥራት አቅጣጫ ማስቀመጡን አንስተዋል፡፡

የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች ተግባራዊ የሆኑ የሪፎርም ሥራዎች ኢትዮጵያን ከውደቀት የታደገ ውጤት ማስመዝገባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ማሞ ምህረቱ በለውጡ ዋዜማ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመንግሥት ሰራተኞች እንኳን ደመወዝ መክፈል በማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በወቅቱ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት በመንግሥት ወጪ በሚገነቡ የመሰረተ-ልማት ሥራዎች ላይ የተንጠለጠለ ስለነበር ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለም እንዲሁ፡፡

የብድር ጫና፣ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲሁም ዝቅተኛ  የወጪ አፈጻጸም  ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እውን መሆን ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው፤ ከለውጡ በፊት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ከማስተዳደር አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደነበረች ይናገራሉ፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ የውጭ ብድር ማግኘት በማትችልበት ደረጃ ደርሳ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ እና ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ በበኩላቸው በተለያዩ መስኮች የተከናወኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ከወዲሁ ውጤታማ ለውጥ እያስመዘገቡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደሚሉት፤ ከለውጡ በፊት "ግብርና መር ኢንዱስትሪ"  የሚል ስትራቴጂ በወረቀት ላይ ከማስቀመጥ ባለፈ ግብርናው ድጋፍ ሲደረግለት እንዳልነበር ገልጸዋል፡፡

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር በማድረግ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ ያስሚን ወሃብረቢ፤ በለውጡ ዋዜማ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ለከፍተኛ ምዝበራና ኪሳራ የተጋለጠ እንደነበር ያብራራሉ፡፡

አቶ ማሞ ምህረቱ፤ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የንግድ ብድሮችን በማስቀረት የእዳ ጫናው ከአገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነጻጸር ከነበረበት 33 በመቶ ወደ 20 በመቶ ዝቅ እንዲል አድርጓል ይላሉ፡፡

በተጨማሪ ከባንኮች የተሰበሰበ ቁጠባን ወደ 1 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር እንዲሁም የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ካለፈው ዓመት በ14 በመቶ ማሳደግ ተችሏል ይላሉ፡፡

ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው በቡና ምርት ብቻ ባለፉት 11 ወራት 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በገቢ አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ እምርታ መመዝገቡንም ነው ወይዘሮ ያስሚን የሚናገሩት፡፡

በጀትን በአግባቡ በመጠቀም ረገድም መሻሻሎች መኖራቸውን እንዲሁ፡፡

ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ቢችልም የኑሮ ውድነቱ አሁንም የኢኮኖሚው ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ይላሉ፡፡

ከዚህ አኳያ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሩ ከሕብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት በተለይ በግብርናው መስክ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመቀነስ በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም