በኦሮሚያ ክልል ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል

120

ሰኔ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የወጣባቸው ከ20 ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ የ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም ሁኔታን በማስመልከት ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም የኦሮሚያ ክልል በበርካታ ተግዳሮቶች መካከል ሆኖ አመርቂ የሚባል የፕሮጀክት አፈጻጸም ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱም በ42 ነጥብ 65 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ ከ20 ሺህ በላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለህዝብ አገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል ነው ያሉት።

ከተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ አነስተኛ የመስኖ ግድቦች፣ ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

አቶ ሽመልስ አክለውም በበጀት ዓመቱ ለመገንባት በዕቅድ የተያዙና ለረጅም ዓመታት ሲጓተቱ የቆዩ ፕሮጀክችን በማጠናቀቅም የመንግሥትን የፕሮጀክት አፈጻጸም ማሻሻል መቻሉን ተናግረዋል።

የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ከ28 ሚሊዮን በላይ የክልሉን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሲሆኑ፤ በመንግሥት በጀት፣ በአጋር አካላት እና በህዝቡ ተሳትፎ መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶችም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት 30 ቀናት ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናሉ ተብሏል።