ህብረተሰቡ በዘመቻው ያደረገው ድጋፍ የጸጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር አቅም ፈጥሯል- የሰላምና ፀጥታ አመራሮች

91

እንጅባራ ኢዜአ ሰኔ 19/2014 ''ህብረተሰቡ በህግ ማስከበር ዘመቻው እያሳየ ያለው ድጋፍ የፀጥታ ችግሮችን ለመቆጣጠር አቅም ፈጥሯል'' ሲሉ የምዕራብ አማራ ዞን የፀጥታ አመራሮች አስታወቁ።

የአማራ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ የምዕራብ አማራ ዞኖችን የህግ የማስከበር ዘመቻ ሂደት ዛሬ  በእንጅባራ ከተማ ገምግሟል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ላቃቸው አብጠው ለኢዜአ እንደገለጹት ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ ከመገባቱ በፊት ከልክ ያለፈ ህገወጥነት ሰፍቶ የህዝቡ አመኔታ ቀንሶ ነበር።

ኢ-መደበኛ ኃይል ህገወጥ ወታደራዊ ስልጠና እስከመጀመር የደረሰና ሌሎች ከባድ ወንጅሎች እየተፈፀሙ በመደበኛው ፖሊስና ሚሊሻ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎት እንደነበር ገልፀዋል።

ህገ ወጦች በፈጠሩት ጫና ህብረተሰቡ ክፉኛ መማረሩንና ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻ መገባቱን ጠቅሰው  ህብረተሰቡ የልዩ ኃይሉ አጋዥ ሆኖ መምጣቱ በአጭር ጊዜ ውጤት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ተናግረዋል።

"ህብረተሰቡ ከመደናገር ወጥቶ ችግሩን እየተረዳ በመምጣቱ አሁን ላይ ህገ-ወጦቹን በተነሳሽነት በማጋለጥ ለፀጥታ ኃይሉ አቅም እየሆነና እየደገፈ ይገኛል"።

መደበኛ ፀጥታ ዘርፍም ህዝብን ይዞ በይቻላል መንፈስና በተቀናጀ መልኩ አቅሙን እያጎለበተ በመምጣቱ ስጋት የሚሆን ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል።

የምዕራብ ጎጃም ዞን ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደነቀ መኩሪያ በበኩላቸው ወደ ዘመቻው ሲገባ ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጎን እንዲቆም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሠራቱን አንስተዋል።

"ህዝቡ የኢ-መደበኛ ኃይሉን ተልእኮ  እየተረዳ በመምጣቱና ለመደበኛው የጸጥታ ሀይል ድጋፍ በማድረጉ አሁን ላይ ከፀጥታ ስጋት ነፃ ሆኖ የልማት ስራዎችን እንዲሰራ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር ተችሏል" ብለዋል።

የህዝቡ ድጋፍ ከዚህ በኋላ በዞኑ መደበኛ የጸጥታ መዋቅር ለሚከናወን የህግ ማስከበር ስራ አቅም የፈጠረ መሆኑን አስታውቀዋል ።

"ዘመቻው በከባድ ዘረፋና ግድያ ለዘመናት ሳይያዙ የነበሩ ወንጀሎችን መያዝ የቻልንበትና ህዝብና መንግስታዊ መዋቅሩ እንዲደማመጥ አጋጣሚ የፈጠረ ነው" ያሉት ደግሞ የባህርዳር ከተማ ሠላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አደራ ጋሼ ናቸው።

"በዚህም ለህዝብ ሥጋትና ህዝብን ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ለማዋል የሞከሩ ጽንፈኛ ኃይሎችን አደጋ ከማድረሳቸው በፊት መቆጣጠር ችለናል" ሲሉም አክለዋል።

ህዝቡ አሁን እያሳየ ባለው አጋርነትና የህግ ይከበርልን አቋም በከተማው መደበኛ ፀጥታ አካላት ዘመቻውን ማከናወን በሚቻልበት ደረጃ ላይ ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ሠላምና ፀጥታ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መንገሻ አውራሪስ በበኩላቸው እንዳስታወቁት በህግ ማስከበር ዘመቻው ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ ያሳደገበት  ነው።

እያንዳንዱ ዞንና ወረዳዎች ከህዝቡ ጋር የውስጥ ፀጥታ ችግሮቻቸውን በራስ መደበኛ ፖሊስና ሚሊሻ መቆጣጠር የሚያስችል አቅም መፍጠር ማስቻሉን አመልክተዋል።

"ዘመቻው ህብረተሰቡን ስጋት ላይ ጥለው የነበሩ ወንጀለኞችን ይዞ ለህግ በማቅረብ የተሻለ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር አስችሏል" ሲሉም አክለዋል።

በህግ ማስክበር ዘመቻው በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በህግ እየተጣራ ክስ እየተመሰረተባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በእንጅባራ ከተማ ዘሬ በተካሄደው የግምገማ መድረክ ከአዊ፣ ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም ዞኖች እንዲሁም ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የፀጥታ ዘርፍ አመራሮች ተሳትፈዋል።



የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም