የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ሀገር ለአደጋ እንዳትጋለጥ አብሮነትን ጠብቀው እንደሚሰሩ ተናገሩ

164

ከሚሴ፣ ሰኔ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ”ሀገር በተንኮለኞች ሴራ ለአደጋ እንዳትጋለጥ አብሮነታችንን በማጠናከርና ሰላማችን በመጠበቅ የድርሻችንን እንወጣለን” ሲሉ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ ዞኖች የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስ በከሚሴ ከተማ ተካሂዷል።

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ኡለማ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ሸህ አብደላህ ሷሊህ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የግል ጥቅመኞች የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሰላምና አብሮነት በመሸርሸር ህብረተሰቡን ወደ ሁከትና ብጥብጥ ለማምራት እየሰሩ ነው።

”አባቶቻችን አጥንትና ደማቸውን ያፈሰሱላት አንድነቷን ጠብቃ የኖረች ሀገራችን በተንኮለኞች ሴራ ለአደጋ እንዳትጋለጥ የሚጠበቅብንን ሁሉ እናደርጋለን” ብለዋል።

በአካባቢው በብሔርና በሃይማኖት ክፍፍል በመፍጠር ህዝብን ለማጫረስ የተደረገ ሙከራ በተቀናጀ ጥረት መክሸፉን አስታውሰው፤ በቀጣይም ለሰላም መረጋገጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የህዝብን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል ችግር እንዳይከሰት በትብብር እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሰሜን ሽዋ ዞን የአንጾኪያ ገምዛ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ አቶ እንድሪስ ገበየሁ በበኩላቸው ሀገር የግል ጥቅም በሚያሳድዱ ባንዳዎች እንዳትፈርስ ተባብረን ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ አለብን ብለዋል።

በንጹሃን ደም ለመነገድ ሁከትና ብጥብጥ የሚፈልጉ ካላትን እንደማይታገሱ ተናግረው፤ ”የአባቶቻችንን የአንድነት፣ አብሮነትና የመከባበር ባህልና እሴት ጠብቀን ኢትዮጵያን እናስቀጥላለን” ሲሉ አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት የተከሰቱትን ዓይነት ቀውሶች እንዳይፈጠሩ መንግስት ህግ የማስክበር ሚናውን መወጣት እንዳለበት ገልጸው፤ ህብረተሰቡም የድርሻውን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

”ሰላም በእያንዳንዳችን እጅ ነው፣ ሁላችንም ለሰላም በቅንጅት በመስራት የጠላቶቻችን ተንኮል ማክሸፍ አለብን” ያሉት ደግሞ በደቡብ ወሎ ዞን የሀርቡ ከተማ የሐይማኖት አባት ሸህ ሰይድ ሀሰን ናቸው።

የሰላም ችግር እንዳይከሰት በቅንጅት መስራትና ወንጀለኞችን ለህግ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ”አካባቢያችንን ነቅተን በመጠበቅ ለአንድነታችንና ለሰላማችን እንሰራለን” ብለዋል።

የኮንፈረንሱ አስተባባሪና የከሚሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ ከድጃ አሊ “በየጊዜው ጠላቶቻችን በሚቀዱልን ቦይ መፍሰስ ሳይሆን ነገሮችን በጥበብ በማለፍ አንድነታችንና ሰላማችንን ጠብቀን አብሮነታችንን ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል” ብለዋል፡፡

በወንድማማች ህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር እየተሞከረ እንደሆነ ጠቁመው፤ ”ሴራው በህዝቡ አስተዋይነት እየከሸፈ ነው” ብለዋል፡፡

ሰላምን ለማረጋገጥ የአባቶችን የመተጋገዝ፣ የመረዳዳትና የአብሮነት ባህልና እሴትን ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የሶስቱም ዞኖች የሐይማኖት አባቶች፣ የሀገር  ሽማግሌዎች፣ አመራሩና ባለድርሻ አካላት አሁን ለመጣው ሰላም የጎላ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤