የጋምቤላ ከተማን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ነዋሪዎች ገለጹ

117

ጋምቤላ፣ ሰኔ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከመንግስትና ከጸጥታ ኃይሎች ጎን በመሆን የጋምቤላ ከተማን ሰላምና መረጋጋት ለማጠናከር እንደሚሰሩ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ አሸባሪው ሸኔና ተላላኪዎቹ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት በጽኑ አውግዘዋል።

ከነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያየት ራሱን የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ተላላኪ ቡድንና አሸባሪው የሸኔ ቡድን ጋር በቅርቡ በጋምቤላ ከተማ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት የአካባቢውን ሰላም ለማወክ መሞከራቸውን አስታውሰዋል።

የቡድኖቹ ሙከራ በጸጥታ ኃይሎችና በህዝቡ የተቀናጀ ጥረት መክሸፉን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሶ ህዝቡ የዕለት ተለት ተግባሩን ማከናወን መጀመሩን ተናግረዋል።

በቀጣይም በከተማውና በክልሉ ያለውን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲሳኩ  የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

አሸባሪዎቹ በጋምቤላ ከተማ ብቻ ሳይሆን በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ የፈጸሙት አረመኔዊ ድርጊት በእጅጉ የሚወገዝ ተግባር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የሽብር ቡድኖቹን እኩይ ሴራ ለማምከን ሁሉም ኢትዮጵያዊ አንድነት ፈጥሮ በጋራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የከተማውን ሰላምና መረጋጋት ይበልጥ ለማጠናከር ጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

መንግስት የሽብር ቡድኖች በንጹኃን ዜጎች ላይ እያደረሱት ያለውን ግድያና ጭፍጨፋ ለማስቆም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀው፤ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤