በአገራዊ ለውጡ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ከህዝብ ጋር ተቀናጅቶ በመፍታት ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን-የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት

127

ሰኔ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)በአገራዊ ለውጡ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ከህዝብ ጋር ተቀናጅቶ በመፍታት የተረጋጋችና ለዜጎቿ የምትመች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሰራለን ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ባካሄደው ስብሰባ በፖለቲካ፣ኢኮኖሚና የሰላም ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተወያይቷል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በተለይ በለውጡ የተቀመጡ አገራዊ ትልሞችን እውን ለማድረግ በየደረጃው ያለው የፓርቲው አመራር በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባለፉት አራት ዓመታት በኢኮኖሚው፣ ፖለቲካና ማህበራዊ መስኮች ላይ ከፍተኛ ስራ መከናወኑን ያነሱት የማእከላዊ ኮሚቴ አባላቱ፤ በሂደቱ የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠልና ፈተናዎችን ተጋፍጦ አሸንፎ በማለፍ አገርን ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አንስተዋል፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ከሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞጢዎስ፤ባለፉት አራት ዓመታት አሳታፊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም ሃሳብ የመግለጽ ነጻነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።

የዴሞክራሲና የነጻነት ልምምድ ጊዜ የሚፈልጉ ሂደቶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በየደረጃው የተለያዩ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ በኢትዮጵያ አምባገነናዊ ስርዓት ነግሶ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ ለዴሞክራሲ ልምምድ የተከፈቱ በሮችን ያለአግባብ በመጠቀም በዜጎች ሰላምና ደህንነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ኃይሎች መበራከታቸውን ገልጸው፤ ይህም የአገራዊ ለውጡ አንዱ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።

የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ሎሚ በዶ እና አቶ ዛዲግ አብርሃ፤አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ አጋጥመው ለነበሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች መፍትሄ መስጠት የቻሉ የሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የሪፎርም ስራዎቹ አገርን ከውድቀት መታደጋቸውን አስታውሰው ባለፉት አራት ዓመትት ያጋጠሙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን ተቋቁሞ እድገት ማስመዝገብ የቻለ ኢኮኖሚ መገንባት ተችሏል ብለዋል።

በፖለቲካው መስክም በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዲስ ምእራፍ በሚባል መልኩ ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባጋራ አገር መምራት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃትን ጨምሮ ለዘመናት አገርንና ህዝብን ሲመዘብሩ የነበሩ ኃይሎች በእነዚህ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ የተለያዩ ሴራዎችን በመፈጸም አገርን አደጋ ላይ ለመጣል ሲሰሩ መቆየታቸውን ወይዘሮ ሎሚ ገልጸዋል፡፡

አቶ ዛዴግ አብርሃ በበኩላቸው በተለያዩ ዘርፎች የሚስተዋሉ የአክራሪነትና የጽንፈኝነት አዝማሚያዎች ባለፉት አራት አመታት የአገር ፈተና ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።

በመሆኑም የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተገኙ ስኬቶችን በማስቀጠልና ያጋጠሙ ፈተናዎችን ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በመፍታት በአገራዊ ለውጡ የተቀመጡ ትልሞችን ለማሳካት በትኩረት እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል።

ዶክተር ጌዴዮን ጢሞጢዎስ፤ መንግስት በቀጣይ የህግ የበላይነትን በማስከበር የኢትዮጵያውያንን ሰርቶ የመልማት እቅድ አውን ለማድረግ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ካጋጠሙ ፈተናዎች መካካል የሰላምና የደህንነት ጉዳይ ተጠቃሽ መሆኑንም አቶ ዛድግ አንስተዋል፡፡ኃይል የመጠቀም ብቸኛ መብት ያለው አካል መንግስት ብቻ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዛዲግ፤ከዚህ አኳያ መሳሪያ በመታጠቅ የህዝብን ሰላም በሚያደፈርሱ አካላት ላይ ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ማዕከላዊ ኮሚቴው በየደረጃው ያለው አመራር ለህግ የበላይነት መከበርና ለማህበረሰብ ትስስር መጠናከር በቁርጠኝነት በመስራት ለለውጡ ስኬት ሚናውን እንዲወጣ አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አመራሩ በዜጎች መካከል ያለው የወንድማማችነትና እህትማማችነት ትስስር እንዲጠናከር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም