ከትምህርታችን በተጓዳኝ ሰላምና አንድነትን መጠበቅ ላይ እናተኩራለን-የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

98

ሰኔ፣ 19/2014 (ኢዜአ) ከትምህርታቸው በተጓዳኝ በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት የሚከፋፍሉ አስተሳሰቦችን በመቃወም ሰላምና አንድነትን መጠበቅ ላይ እንደሚያተኩሩ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።

በዩኒቨርሲቲው የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል  የ4ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ናትናኤል ኤሊያስ እንዳለው ባለፉት ዓመታት የተዘሩ ከፋፋይ አስተሳሰቦች ዛሬ ላይ የዜጎችን ውድ ህይወት እያሳጡ ነው።

”ያለፉ አስቸጋሪ ጊዜያቶችን በአንድነትና በመተሳሰብ በማለፍ  ብዙ ድሎች ማስመዘገባችንን ታሪክ ምስክር ነው” ያለው ተማሪ ናትናኤል፤ አሁን እንደ ሀገር በገጠመው ፈተና እጅ መስጠት እንደማይገባ ተናግሯል።

ከፋፋይ አስተሳሰቦች የአብሮነትና የሀገር አንድነት ጸር መሆናቸውን ጠቁሞ፤ የእኩይ  ዓላማ አራማጆችን ሀሳብና  ተግባር ባለማስተናገድና ለጋራ ጠላቶች በጋራ በመቆም ለሀገር ሰላምና አንድነት መስራት እንደሚገባ አመልክቷል።

ጠላቶቻችን የነገ ተስፋችንን ለማጨለም እየጣሩ ነው ያለው ናትናኤል፣  ”ወጣቶችና ተማሪዎች ነገሮችን በሰከነ መንፈስ  ማየት ይገባል” ብሏል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ  የሁለተኛ አመት የምህንድስና ተማሪ ቤተልሔም አበራ “ከዚህ ቀደም እንደ ሀገር የመጡብንን በርካታ ፈተናዎች በፅናት ተቋቁመን ያለፍነው አንድነታችንን በማጠናከር ነው” ብላለች።

የኢትዮጵያን ሰላም መሆን የማይፈልጉና እድገቷን በተለያየ መንገድ ሊገቱ የሚፈልጉ አካላትን ዓላማ ማክሸፍ የሚቻለው በአንድነትና በመተባበር መቆም ሲቻል መሆኑን ተናግራለች።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዘርና ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ ወንጀል እየፈጸሙ ባሉ አካላት ላይ መንግስት የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቃለች።

በህዝብ መካከል የቆየውን የአብሮነት እሴት በመሸርሸር በሀገር ላይ አለመረጋጋትን ለማስፈን ለሚደረገው ጥረት እድል መስጠት እንደማይገባ የተናገረው ደግሞ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍል 3ኛ ዓመት ተማሪው ስዩም ታፈሰ ነው።

ለዘመናት አብሮ የኖረው ማህበረሰብ  በወንድሙና እህቱ ላይ አሰቃቂ ወንጀል ሲፈጸም ለምን ብሎ ሊጠይቅና  እኩይ ድርጊቱን ሊያወግዝ እንደሚገባ ተናግል።

”አባቶቻችን የቋንቋና ሌሎች ልዩነቶችን እንደ ውበት በመውሰድ የውስጥ አንድነታቸውን በመጠበቅ የጠላትን ሴራ ሲያከሽፉ ቆይተዋል” ያለው ተማሪ ስዩም፤ የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ በጎ ተግባር በመማር እርስ በእርሱ ሊረዳዳበት እንጂ ሊጎዳዳበት እንደማይገባ አመልክቷል።

” የዘር ፖለቲካ አሽቀንጥረን በመጣል በመደጋገፍና በመተሳሰብ የሀገርን ሉዓላዊነት ልክ እንደ ትናንቱ ልናስጠብቅ ይገባል” ብል ።

ተማሪዎቹ በዩኒቨረሲቲ ቆይታቸው የሁሉንም ማህበረሰብ ባህልና ወግ በማክበርና አንዱ ከአንዱ በመማር  ከትምህርታቸው በተጓዳኝ ሰላምና አንድነትን መጠበቅ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።