“የቤተሰብ ንግድ” የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ውጤታማ ኢንተርፕራይዝ እንዲፈጠር ያስችላል

195

ሰኔ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)“የቤተሰብ ንግድ” በሀገሪቷ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር በመቅረፍ ውጤታማ እና ተሻጋሪ ኢንተርፕራይዝ እንዲፈጠር እንደሚያስችል ተገልጿል።

“የቤተሰብ ንግድ ለኢተርፕራይዞች ውጤታማነት እና ቀጣይነት ያለው ፋይዳ” በሚል የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ስልጠና በጅግጅጋ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

የመድረኩ ዋና ዓላማ በስራ ዕድል ፈጠራ አፈፃፀም መመሪያና የቤተሰብ ንግድ አደረጃጀት ሰነድ ለሚመለከታቸው አካላት ለማስተዋወቅ ነው ተብሏል።

በወቅቱ የቀረበው ሰነድም በቤተሰብ በመደራጀት የሚፈጠረው የንግድ ዓይነት በኢትዮጵያ ማህበራዊ መሰረት ያለውና ውጤታማ የንግድ ዓይነት መሆኑ ተመላክቷል።

ከሶማሌ ክልል፣ሀረሪ ክልልና ድሬደዋ አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል ተቋማት የስራ እድል ፈጠራ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።

በመድረኩ ላይ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ፤የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሓሺ እና የሶማሌ ክልል ስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ገይድ ተገኝተዋል።

ስልጠናው ለአምስት ቀናት የሚቆይ መሆኑ ታውቋል፡፡