አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት የኦሮሞን ህዝብ አይወክልም – ነዋሪዎች

246

ነገሌ ሰኔ 18/2014(ኢዜአ)— አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ በንጹሃን ላይ የፈጸመው ጥቃት የኦሮሞን ህዝብ የማይወክል አፀያፊ ድርጊት ነው ሲሉ የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ መንግስት በሽብርተኛው ሸኔ ላይ እየወሰደ ያለውን የህግ ማስከበር እርምጃንም እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

የነገሌ ከተማ  03 ቀበሌ ነዋሪ  መቶ አለቃ ንጉሴ ሰለሞን  እንዳሉት በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ላይ በተፈጸመው አረመኔያዊ ጥቃት ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቡድኑ ምንም በማያውቁ ሴቶችና ህጻናት ላይ የፈጸመው ጥቃት ” በመንግስት እየተወሰደበት ባለው እርምጃ ተስፋ መቁረጡንና ዓላማ የሌለው ገዳይ መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን” ጠቁመዋል፡፡

ችግሩ ሁላችንንም የሚመለከት በመሆኑም ከመንግስት ጎን ሆነን መረጃ በመስጠትና በሚያስፈልገው ሁሉ በመተባበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድርጊቱን ልናስቆም ይገባል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የከተማው  ነዋሪና የሀገር  ሽማግሌ አቶ  ዲዳ ገልገሎ “ኦሮሞ  አቃፊና ደጋፊ  እንጂ ገዳይና ጨፍጫፊ እንዳልሆነ እሴቶቹና ዓለም በሙሉ ይመሰክራል” ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ ግጭትና አለመግባባት ሲፈጠር የሰው ህይወት ከመጥፋቱ አስቀድሞ ተወያይቶና ተመካክሮ የሚፈታበት የራሱ የሆነ ባህላዊ ስርዓት ያለው መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ የሽብር ቡድኖች የአሮሞን ህዝብ የማይወክሉና ባህሉንም ጠንቅቀው የማያውቁ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በባህልም ሆነ በእምነት “የሰው ህይወት ማጥፋት ፍጹም አሳፋሪና ወራዳ ተግባር እንደሆነ የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ይህንን ድርጊት አይፈፅምም፣ የፈጸሙትንም ይቃወማል” ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ሸኔ በንጹሃን ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆም በመንግስት የሚወሰደውን  እርምጃ የሚደግፉት በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል አቶ ዲዳ ፡፡

የከተማው 03 ቀበሌ ነዋሪ ፓስተር አለማየሁ ገልገሎ በበኩላቸው “ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ህይወት ማጥፋት እንስሳዊ ተግባር” መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት በማስተማር፣ ህዝብ ደግሞ መረጃ በመስጠት፣ እንዲሁም  መንግስት  የህግ የበላይነትን በማስከበር “ተባብረን መሰል ድርጊቶች ዳግም እንዳይፈፀሙ ልናስቆም ይገባል” ነው ያሉት፡፡

ሽብርተኞች የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፉ በመሆኑ በመንግስት  የሚወሰደው  የህግ ማስከበር ስራ  ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

የሰው ህይወት ማጥፋት ከፈጣሪ ከመጣላትና ሀገር ከማፍረስ የዘለለ ምንም አይነት የፖለቲካ ትርፍ እንደማያስገኝም ታሪክ ይነግረናል ይላሉ ፓስተር  አለማየሁ፡፡

አሸባሪዎች ንጹሃን ላይ የሚያደርሱትን  ጥቃት ለማስቆም በሃይማኖትና  በብሄር ሳንከፋፈል አንድ  ሆነን  በመነሳት ማስቆም አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡

የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ዋሪዮ ኮቶላ ጥቃቱን ለማስቆም ከመንግስት ጎን ሆነን መረጃ በመስጠት የህግ ማስከበር እርምጃውን እንደግፋለን ብለዋል፡፡

በምእራብ ወለጋ በአዛውንቶች፣ ሴቶችና ህጻናት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ታሪክ ይቅር የማይለው የሽብር ተግባር በመሆኑ እንዳይደገም ሁላችንም ሀላፊነት አለብን በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።