በወላይታ ዞን ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ96 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተዘጋጅተዋል

173

ሶዶ ሰኔ፣ 19/2014 (ኢዜአ) በወላይታ ዞን ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ96 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ ።

የዞኑ ነዋሪዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ኦርሳንጎ ችግኞቹ በመንግስትና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተሳትፎ በሚመሩ 295 የችግኝ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ከ22 በላይ የከተማ አስተዳደሮችና ገጠር መዋቅሮች ለችግኝ ተከላ የሚሆኑ ቦታዎች ልየታና የጉድጓድ ቁፋሮ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ገበያ ተፈላጊነቱ ከፍ እያለ የመጣውን አቮካዶ በብዛት ለመትከል መታቀዱን ገልጸዋል።

የቡና ማሳ ጨምሮ ሌሎች ተክሎችን ለመጠበቅና ለጥላነት የሚውሉ እንደ ዋንዛ፣ ብሳና፣ ወይራና ቀርከሃ የመሳሰሉ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።

መርሃ ግብሩ የሀይማኖት ተቋማትን ጨምሮ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተሳትፎ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት ከ360 በላይ የንዑስ ተፋሰሶች የተተከሉት ችግኞች ከ84 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ መርሃ ግብሩ እያስገኘ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት በችግኝ ተከላው እያሳየ ያለውን ተሳትፎ በመንካበከብ እንዲያስቀጥለው አቶ አለማየሁ ጠይቀዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት የወላይታ ዞን የሶዶ ከተማ ነዋሪ ወንድሙ ጋጃ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ላይ መሳተፍ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው መሆኑን ገልጸው፡ የመሬት ለምነት በመመለስ ግብርናውን ውጤታማ ያደርገዋል"ብለዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ አንስቶ በመኖሪያ ግቢያቸውና በመስሪያ ቤታቸው ችግኞችን ተክለው እንክብካቤ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያዊያን አረንጓዴ ዐሻራቸውን እንድናሳርፍ የሚቀርብልንን ጥሪ ተቀብለን የነገ ተስፋችንን ማሳመር ይገባናል'' ብለዋል።

የሶዶ ዙሪያ ቶሜ ጌሬራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ዴኣ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ መሳተፍ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን አመልክተዋል።

የውሃና የአየር ብክለትን በመቀነስ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጡን በማስተካከል የግብርና ዘርፉን ማሻሻል እንደሚቻል አመልክተው፣በዚህም የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በማሳቸው ከ120 ችግኞች በላይ መትከላቸውን ያስታወሱት አቶ ሀብታሙ፤ ለችግኞቹ በሚያደርጉት ክትትልና እንክብካቤ አብዛኛዎቹ መፅደቃቸውን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ከ40 በላይ ችግኞች በመትከል አካባቢያቸውን ከጎርፍ አደጋ እንዲሁም ከመሬት መንሸራተት ለመታደግ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የዳሞት ጋሌ ወረዳ ዶጌ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መብራት ሎሃ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በተለይ ለምግብነት የሚሆኑ ችግኞችን በመትከል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በመሆኑም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ የፍራፍሬ ችግኞችን በመኖሪያቸውና በመስሪያ ቤታቸው ለመትከል ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓም እንደሚጀምር የመምሪያው መረጃ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም