በዞኑ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች አሸባሪው ሸኔ በንፁሀን ዜጎች ላይ የፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በፅኑ አወገዙ

96

ፍቼ፤ሰኔ 18 ቀን 2ዐ14 (ኢዜአ) አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ሰሞኑን በንፁሀን ዜጎች ላይ የፈፀመው ግድያ ሕዝብን በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያለመ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ በፅኑ እንደሚያወግዙት በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስታወቁ፡፡

አሸባሪው ሸኔ ንፁሀን ዜጎችን በግፍ በመጨፍጨፍ የፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የትኛውንም ብሔር የማይወክል የሽብርተኝነት ተግባር መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ገልጸዋል።

በኦሮሞ ሕዝብ ስም በመነገድ ከኦሮሞ ሕዝብ የአቃፊነት፣ የመተባበርና የአብሮነት የአንድነት ባህላዊ እሴት ያፈነገጠ አስነዋሪ ተግባር በመሆኑ በፅኑ እንደሚያወግዙት ተናግረዋል።

በፍቼ ከተማና አካባቢዋ የአባ ገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ አቶ ዘነበ ቱፋ "ድርጊቱ በምንም መልኩ ኦሮሞን የማይወክል የኦሮሞን ሕዝብ ፍላጐት የማይገልፅ ተግባር ነው" ብለዋል።

የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ማንኛውንም ብሔር ብሔረሰብ በውስጡ ማቀፍ ነው ያሉት አባ ገዳ ዘነበ ለዚህም በክልሉ ያሉ ስብጥር ነዋሪዎችን ለአብነት መመልከት ይበቃል ነው ያሉት።

ወጣቱም ወደ አስነዋሪ ድርጊት እንዳይገባ የአባቶቹን የገዳ ሥርዓት ማስተማር፣ ማንነቱን እንዲያውቅና በማንነቱ ኮርቶ እራሱንና ሀገሩን እንዲጠብቅ መስራት እንደሚገባም መክረዋል።

በንጹሃን  ወገኖች ላይ በደረሰው ጉዳት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ከጉዳቱ የተረፉ ወገኖችን በማቋቋምና በማፅናናት የበኩላቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የፍቼ ከተማ ቀበሌ ዐ3 ነዋሪና የባህልና እሴት ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዳመና አበራ በበኩላቸው በምዕራብ ወለጋ በአሸባሪው ሸኔ የተፈፀመው የጅምላ ግድያ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ የተፈጸመው ድርጊት የኦሮሞንም ሆነ የትኛውንም ሕዝብ የማይወክል የአካባቢውን ኅብረተሰብ መልካም ገፅታ ለማጠልሸት ያለመ ሴራ ነው ብለዋል።

ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቱ የኦሮሞን ሕዝብ በማጋጨት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የውጭ ኃይሎችና የአሸባሪው ህወሓት እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል ሴራ ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።

የኦሮሞ ሕዝብ ከየትም ቦታ ቢመጣ ሰው በመሆኑ ብቻ በእኩልነት አቅፎ በአብሮነት የመኖር ባህለዊ እሴት፣ ወግና ሥርዓት ያለው መሆኑንም ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ባልደረባ ኮማንደር ደረጀ ፈጠነ እንዳሉት የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን ባህልና ሥርዓት ለዓለም ያስተዋወቀ አብሮ በመኖር፣ በመቻቻል በእንግዳ ተቀባይነት የሚታወቅ ነው።

አሸባሪ ሸኔ ኦሮሞን እየገደለ፣ እያፈናቀለ፣ እየዘረፈና አግቶ ወስዶ እያሰቃየ ያለ ዓላማ የሌለው የኦሮሞ ሕዝብ ጠላት ነው ብለዋል።

በየትኛውም መስፈርት ንፁሀንን መግደል ተሰሚነትም ሆነ ተቀባይነት የማያስገኝ መሆኑን ጠቁመው ድርጊቱ የኦሮሞን ሕዝብን መልካም ገፅታ ለማጠልሸት ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

ሕዝቡ በአንድነት ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ ይህን መሰል ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዳይደገም የሽብር ቡድኑን በፅናት እንዲታገልም ጠይቀዋል።

እንዲሁም አሸባሪውን ሸኔን በሕብረት ከማጥፋት ጎን ለጎን የእኩይ ድርጊቱ ተጐጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም