የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርአት እና የማስረጃ ረቂቅ ህግ ሚዛን የጠበቀና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያጠናክር ነው - ፍትህ ሚኒስቴር

242

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርአት እና የማስረጃ ረቂቅ ህግ ሚዛን የጠበቀና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያጠናክር መሆኑን ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ።

በኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረውን የወንጀል ሕግ ለማሻሻል በተዘጋጀው የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርአት እና የማስረጃ ህግ ረቂቅ ህግ በተመለከተ ከፍትህና የዳኝነት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ውይይት አድርገዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ የፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከፍትህ ተቋማቱ ባለሙያዎች ጋር በረቂቁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጓል።

በኢትዮጵያ ከ60 ዓመት በላይ ስራ ላይ የነበረው የወንጀል ሕግ አሁን ካለው ሕገ-መንግስት ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑ ተነስቷል።

የተዘጋጀው ረቂቅ ህግ ለሚፈጸሙ ውስብስብ ወንጀሎች እልባት ለመስጠት እንደሚያስችል ተገልጿል።

በረቂቁ ላይ ከ10 ዓመት በላይ በየደረጃው የፍትህ አካላት ሲወያዩበትና ለማሻሻል ሲሰሩበት የቆየ እና ሰፊ ግብዓት የተሰባሰበበት መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምአንተ አግደው ገልጸዋል።

በ1949 ዓ.ም ህጉ ሲወጣ ይፈጸም የነበረው ወንጀል የተለየ እና አሁን የሚፈጸመው ወንጀል እየተወሳሰበ መምጣን ጠቅሰው፤ አዲሱ ረቂቅ ህግ ሚዛን የጠበቀና የሰብዓዊ መብቶችን ጥበቃ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

በወንጀል ፍትህ ስርዓት የማህበረሰብን ተሳትፎ የሚያጠናክር፣ የወንጀል ጉዳዮችን ሰላማዊ ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ እንዲሁም ለወንጀል ጉዳዮች ዘለቄታዊ ዕልባት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል።

በረቂቁ የዕርቅና የጥፋተኝነት ድርድር የተካተተበት መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሰለሞን አረዳ በረቂቅ ሕጉ የፍትህ አካላት በማለት ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ እና ዐቃቢ ህግ የራሳቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲተገብሩ የሚያስችል አሰራር ቢካተት ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ የተገኙት ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ፤ ምርመራን ዐቃቢ ሕግ ይመራል የሚለው ከፖሊስ የምርመራ ስራ ጋር ስለሚደራረብ ቢሻሻል ሲሉ ጠይቀዋል።

የተጠርጣሪ ቤት ለመበርበርና ለመያዝ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ የሚለው አደገኛ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ስለሚያዘገይ እንደየአስፈላጊነቱ በሚል ቢሻሻል የሚልም ሀሳብ አቅርበዋል።

ከኢትዮጵያ ሕግባለሙያዎች ማህበር እና ጠበቆች ማህበር የተሳተፉት ዘላለም ክፍሌ ረቂቁ ለረጅም ዘመናት የሚያገለግልና የተከሳሽን መብት ለመጠበቅ የሚያስችል መሆን አለበት ብለዋል።

በምክር ቤቱ የሕግ፣ የፍትህ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ኢሳ ቦሩ በረቂቁ ዙሪያ በርካታ ግብአቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም