የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ የጎላ አስተዋዕጽኦ አለው - ፍትሕ ሚኒስቴር

288

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ የጎላ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ አፈፃጸም ክትትል ሪፖርት ከተደረገባቸው የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና ጉምሩክ ኮሚሽን አመራርና ሰራተኞች ጋር ውይይት አካሂዷል።

በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው ውይይት የፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ምንነት እና የየተቋማቱ የአፈፃጸም ክትትል ሪፖርት ለውይይት መነሻነት ቀርቧል።

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቃዱ ፀጋ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የዜጎችን አገልግሎት አሰጣጥ ፍትሃዊ ለማድረግ በርካታ የህግ ማሻሻያ ማድረጓን ገልጸዋል።

የሚወጡ ህጎችን ተፈፃሚነት ለማረጋገጥም የፍትህ ሚኒስቴር ተልዕኮና ኃላፊነት ወስዶ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ አገልገሎት አሰጣጥን ፍትሃዊ ለማድረግ ከወጡ ህጎች መካከልም "የፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012" አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

አዋጁም ዜጎች የሚመሩበትን መመሪያ በመገንዘብ የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ላይ ቅሬታ ካላቸው እስከ ፍርድ ቤት ድረስ በማቅረብ ፍትሃዊ ውሳኔ እንዲያገኙ የሚያደርግ እውቅና መስጠቱን ጠቅሰዋል።

የፌደራል ተቋማትም አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚያወጡትን ነባርም ሆነ አዲስ መመሪያ ለፍትህ ሚኒስቴር እንዲያስመዘግቡ፤ ዜጎችንም ተሳትፎ እንዲያደርጉበት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የዜጎችን ተሳትፎን በተሟላ መልኩ ከማሳደግ አንፃር ውስንነቶች ቢኖሩም ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው ሀገራቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ረገድ አዋጁ ትልቅ አስተዋዕኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

በሚኒስቴሩ የፌደራል ሕጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክተሯ ትብለጥ ቡሽራ፤ የፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ተቋማት በዜጎች መብት ላይ ጣልቃ በሚገቡበት ወቅት በህግ ለመዳኘት የወጣ አዋጅ መሆኑን ገልጸዋል።

ዜጎች በአስተዳደር መመሪያና ውሳኔ ላይ በደል ሲደርስባቸው ካሳና ፍትህ እንዲያገኙ ለማስቻልም አዋጁ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል።

አዋጁ ተግባራዊ ከሆነ ሁለት ዓመታትን ቢያስቆጥርም በተቋማት በኩል ያለው አፈፃጸም ግን ክፍተት እንዳለበት አንስተዋል።

በቀጣይም ተቋማት የሚያጋጥሟቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት አዋጁን ተንተርሰው በሚያወቷቸው መመሪያዎች ላይ መፍታትና ውሳኔ ማሳለፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዐቃቢ ህጉ ብርሃኑ ወርቄ፤ የፌደራል ተቋማት አዋጁን በምን አይነት መልኩ እየተገበሩት እንደሚገንኝ የክትትል ስራ ሲከናወን መቆየቱን ገልጸዋል።

በተደረገው የክትትል ግምገማም የተወሰኑ ክፍተቶች ቢስተዋሉም ነባርና አዲስ መመሪያዎችን በማውጣት ከባለድርሻ አካላትና ተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን በበጎ አንስተዋል።

የፌደራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የወጣ ሲሆን አዋጁም ዜጎች መብትና ግዴታቸውን ተረድተው የሚያጋጥሟቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም