ኮሌጁ ለ5ኛ ዙር በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

150

ነገሌ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የነገሌ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለ5ኛ ዙር  በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በደረጃ አራት ያሰለጠናቸውን 229 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡

ተመራቂዎቹ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ በግንባታ፣ በእጽዋት ሳይንስና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ መሆናቸውን የኮሌጁ ዲን አቶ ነጌሳ ጂማ ገልጸዋል።

በኮሌጁ ላለፉት አራት አመታት በንድፈ ሀሳብና በተግባር ትምህርት ሰልጥነው ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 152 ሴቶች እንደሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ኮሌጁ አሁንም የመግቢያ መመዘኛውን ያሟሉ 490 ተማሪዎችን ተቀብሎ በእነዚሁ የትምህርት ዘርፎች በማሰልጠን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከነዚህም በተጨማሪ የተማሪዎችን ቅበላ አድማሱን በማስፋት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት አዳዲስ የሽመናና የልብስ ስፌት ስልጠና እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

በምረቃው ላይ የተገኙት የጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ነጋሽ ቡላላ ሀገር የሚገነባው በሰለጠ የሰው ሀይል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ነገሌን ጨምሮ በጉጂ ዞን በብዙ ሚሊዮን ብር የተገነቡ 8 የተለያዩ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች አሁንም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብለው በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

መንግስት የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊ የገቢ ማስገኛ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ተወካዩ፤ ወጣቶች በኮሌጆች እራሳቸውን በስልጠና አበልጽገው በሀገር ግንባታ ልማትና እድገት ለመሳተፍ የሚያበቃቸውን እውቀት እንዲጨብጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም