በ300 ወረዳዎች የ10 ዋና ዋና ሰብሎች ልማት በኩታ ገጠም እየተከናወነ ነው

126

አዳማ፣ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ 300 ወረዳዎች አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የአስር ዋና ዋና ሰብሎች ልማት በኩታ ገጠም እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ገለጸ።

ኤጀንሲው በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የኩታ ገጠም ሰብል ልማት ያለበትን ሁኔታ የዳሰሰ የምክክር መድረክ በአዳማ እያካሄደ ይገኛል።

በኤጀንሲው የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ሲኒየር ዳይሬክተር ዶክተር ዳኛቸው ሉሌ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የግብርና ምርቶችን የውጭ ተፈላጊነት ለማሳደግ የግብርና ልማቱ ገበያ ተኮር መሆን አለበት።

በኩታ ገጠም በማልማት የምርት ጥራትና ብዛትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ስንዴ፣ ጤፍ፣ የቢራ ገብስ፣ በቆሎ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን በኩታ ገጠም ማልማት መጀመሩን ጠቅሰዋል።

ከአትክልትና ፍራፍሬ ውስጥ ሽንኩርት፣ ቲማትም፣ ሙዝ፣ አቮካዶና ፓፓያ በኩታ ገጠም እየለሙ ይገኛሉ ብለዋል።

300 ወረዳዎች ውስጥ የኩታ ገጠም ሰብል ልማት መጀመሩን ጠቅሰው፤ በኩታገጠም የእርሻ ልማት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህም በዋና ዋና ሰብሎች ምርትና ምርታማነት ዕድገት ላይ ተስፋ ሰጪ ጅምር ውጤቶች መኖራቸውን አመልክተዋል።

በሙከራ ደረጃ የተጀመረውን የኩታ ገጠም የእርሻ ልማት ስራ በሁሉም የአገሪቱ ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ገበያ ድረስ ያለው ሂደት የባለሙያ ክትትልና ድጋፍ እንዳለው ገልጸው፤ ትርፍ በማምረት የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ጥራቱን የጠበቀ በቂ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በኤጀንሲው የግብይትና አግሮ ቢዝነስ ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መስፍን በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የአርሶ አደሩን የገበያና የምርት ማከማቻ ችግር ለመቅረፍ የምርት ማሰባሰቢያ ማዕከላት በኦሮሚያና አማራ ክልል ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የደላሎችን ሰንሰለት በማስወገድ አርሶ አደሩ ምርቱን ቀጥታ ለሸማቹ እንዲያቀርብ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም