በሶማሌ ክልል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች የኮሮና መከላከያ ክትባት ተሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች የኮሮና መከላከያ ክትባት ተሰጠ

ጅግጅጋ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) በሶማሌ ክልል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ለሚበልጡ ሰዎች ሶስተኛው ዙር የኮሮና መከላከያ ክትባት መሰጠቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ላለፉት አስራ አምስት ቀናት የተካሄደው የክትባት መርሃ ግብር ከታቀደው ውስጥ በአብዛኛው መከናወኑን በቢሮው የእናቶች እና ሕፃናት ጤና ቡድን ተወካይ አቶ መሀመድ መሀሙድ ተናግረዋል ።
መከላከያ ክትባቱን ለ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ለመስጠት የተያዘው ግብ ለማሳካት በተጨማሪ ለ4 ቀናት እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
በክልሉ ሲሰጥ የቆየውና አሁንም የቀጠለው የክትባቱ መረሃ ግብር በክልሉ በሚገኙ ስድስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ፣ የተለያዩ የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ 500 ጊዜያዊ ተንቀሳቃሽ ድንኳኖች መሆኑን ገልጸዋል።
በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ 1 ሚሊዮን 415 ሺህ 457 ሰዎች መከተባቸውን ነው አቶ መሀመድ ያስታወቁት።
ክትባቱን ከወሰዱት መካከል 648 ሺህ 541 ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከክትባቱ በተጓዳኝ የጤና ባለሙያዎቹ ለህብረተሰቡ ስለ ኮሮና በሽታ ምልክቶችና መተላለፊያ መንገዶች እንዲሁም ስለ መከላከያው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጅግጅጋ ከተማ የኮቪድ -19 ቀንቀሳቃሽ የክትባት ማዕከል ባለሙያ ሲስተር ሙና በሺር ናቸው።
ባለሙያዋ እንዳሉት፤ አብዛኛው ማህበረሰብ ኮሮና እስካሁን አለመጥፋቱን በመረዳት በሶስተኛው ዙር መረሃ ግብር በራሱ ተነሳሽነት ክትባት እየወሰደ ይገኛል።
በማዕከሉ ክትባት ሲወስዱ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ መሀመድ ረሼድ አደን ሐሰን በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ሁለት ዙሮች የወሰዱት ክትባት ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ችግር እንዳልፈጠረባቸው አስታውሰዋል።
ሌላውም ህብረተሰብ እራሱን ከበሽታው ለመከላከል የተመቻቸለትን ክትባት በወቅቱ እንዲወስድ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ