አካዳሚው የሚያከናውናቸው ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች በስፋት ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል- የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ

194

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የሚያከናውናቸው ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች በስፋት ተግባር ላይ ሊውሉ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ ተናገሩ።

ሰባተኛው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።

በሲምፖዚየሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጀላ መርዳሳ፤ አካዳሚው የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ጥናታዊ ጽሁፎች እንዲሰሩ ማድረጉን አድንቀዋል።

በመሆኑም በአካዳሚው የሚሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ወደ ተግባር የሚለወጡበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ መስራት ይገባል ብለዋል።

አካዳሚው የሚያከናውናቸው ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች በስፋት ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል ነው ያሉት።

የጥናት ውጤቶችን በየጊዜው በመገምግም ጠንክራ ጎኖችን ለማጠናከር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ አንበሳው እንየው፤የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት ሶስት ዓላማዎች መካከል ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግና ማማከር አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረትም አካዳሚው ከ2006 እስከ 2012 ዓ.ም 41 የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎችን በተለያዩ ባለሙያዎች እንዲሰሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

አካዳሚው ካሰራቸው ጥናታዊ ስራዎች መካከል የተወሰኑት በአካዳሚው ተተግብረው ጥሩ ውጤት መታየቱንም ጠቅስዋል።

በአትሌቶች የስፖርት ስልጠና ላይ የተሰራ ጥናት በአካዳሚው የስፖርት ሰልጣኞች መተግበሩን ለአብነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ብዙም በውጤት የማትታወቅባቸው የቴኳንዶ ስፖርትና የሜዳ ላይ አትሌቲክስ ተግባራት አሁን ላይ ተስፋ ስጪ ውጤቶች ታይተዋል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተቀዛቅዞ የነበረው የቦክስ ስፖርት ላይ መነቃቃት መፍጠሩን ነው የተናገሩት።

ሌሎች የስፖርት ማህበራት፣ ክለቦችና የሚመለከታቸው ሁሉ አካዳሚው የሚያሰራቸውን ጥናቶች ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

ለዚህም የማማከር አገልግሎት ለመስጠት አካዳሚው ዝግጁ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።

በዛሬው ሲምፖዚየም በስፖርት አስተዳደር፣ በእግር ኳስ ስልጠና፣  በእግር ኳስ ዳኝነትና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ 15 ጥናታዊ ስራዎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

በሲፖዚየሙ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች፣ የስፖርት ምሁራንና ተመራማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።