የብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በምእራብ ወለጋና በጋምቤላ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ

113

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በምእራብ ወለጋና በጋምቤላ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አወገዙ።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን በአዲስ አበባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በምእራብ ወለጋና በጋምቤላ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

በቀጣይ የጥቃቱን ተጎጂዎች ከመደገፍ ጎን ለጎን ህግ የማስከበር ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኮሚቴው አባልና የመስኖና ቆላማ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ ሸኔና ሌሎች አሸባሪ ኃይሎች ሀገርን ለማፍረስ ብዙ ጊዜ ሞክረው ሳይሳካላቸው ሲቀር በንጹሃን ላይ የፈፀሙት ጭፍጨፋ  እጅግ አሳዛኝ ነው ብለዋል።

አሸባሪ ኃይሎቹ በተቀናጀ መንገድ የፈጸሙትን ዘግናኝ እልቂት የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ በፅኑ ማውገዙን ነው የገለጹት።

ሌላኛው የኮሚቴው አባል ግርማ አመንቴ፤ ማዕከላዊ ኮሚቴው በንጹሃን ላይ የተፈፀመውን እልቂት  ማውገዙን በማንሳት፤ ፅንፈኞች የሀገሪቱን አብሮ የመኖር እሴቶችና የሰው ልጅ ሞራላዊነትን የሚንድ አስነዋሪ ድርጊት ፈፅመዋል ነው ያሉት።

ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ልብ የሚሰብር ነው ያሉት ሌላኛው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ዛዲግ አብርሃ ናቸው።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ኡሞድ ኡጁሉ፤ ሸኔ፣ እራሱን የጋምቤላ ነጻነት ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድንና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ሰሞኑን በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈፀሙት ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሁሉንም ያሳዘነ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጊቱን የፈጸሙ ኃይሎች ላይ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ህግ የማስከበር እርምጃው እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው የብልፅግና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባም እየተወሰዱ ያሉ ህግ የማስከበር እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዴዮን ጢሞቲዎስ፤ በየአካባቢው ያሉ አደረጃጀቶች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመናበብ በአሸባሪ ሃይሎች ጋር የሚወሰደው እርምጃ እንዲጠናከር ማዕከላዊ ኮሚቴው መግባባት ላይ ደርሷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚና የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ፍስሐ ይታገሱ፤ የሽብር ቡድን አባላትን ተከታትሎ እርምጃ መውሰድና ለህግ ከማቅረብ ባሻገር፤ ህዝቡም በተደራጀ መንገድ እራሱን የሚከላከልበትን መንገድ መፈለግ እንደሚገባ በስብሰባው መነሳቱን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አማካሪና የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ማሞ ምህረቱ፤ ፅንፈኝነትና አክራሪነትን ለማክሰም በትኩረት እንዲሰራና የፀጥታ ሃይሉም ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በተጠናከረ መንገድ እንዲጠብቅ አቅጣጫ ተቀምጧል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ እና የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሎሚ በዶ፤ ጸረ ሰላም ሃይሎችን በመዋጋትና ለሰላም ዘብ በመቆም ሁሉም ዜጋ የሰላም አምባሳደር መሆን አለበት ብለዋል።

"አመራሩም የሚናገረውን የሚተገብርና አንድ መሆን አለበት" በማለት ለዚህም በአካባቢ ሳይታጠር የፀጥታ ችግሮችን  በጋራ መፍታትና ተጠያቂነትን በአግባቡ ማረጋገጥ ይገባል ነው ያሉት።

ማዕከላዊ ኮሚቴው በተለያዩ ወሳኝ አገራዊ አጀንዳዎችና የፓርቲ ሥራዎች ላይ ተወያይቶ በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት ላይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም