በጋምቤላ ክልል ለ310 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጠ

131

ጋምቤላ፣ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል እየተገባደደ ባለው የበጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 310 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።


የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከል 290 ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ሲሆን ከመካከላቸውም ከ70 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መሰጠቱ ተገልጿል።


ኮሚሽነር ዶክተር ሎው ኡቡፕ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱት በግብርና፣ በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት ነው።


በዚህም በክልሉ በበጀት ዓመቱ እስከ ግንቦት ወር ድረስ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 310 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።


ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የተሻለ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንደነበር የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ ለእዚህም በቅርቡ አሸባሪው ሸኔ እና ጋነግ ከፈጠሩት የጸጥታ ችግር በስተቀር በክልሉ የተረጋጋ ሰላም መኖሩና ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።


እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ፣ በክልሉ በግብርና ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ከ290ቹ ባለሃብቶች መካከል ከ70 በላይ ለሚሆኑ ባለሃብቶች ከ26 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ተሰጥቷል።


በበጀት ዓመቱ በሁሉም ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ ባለሀብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ ከ27 ሺህ 850 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።


በበጀት ዓመቱ በግብርናው ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱት ውስጥ 50 የሚሆኑት ወደ ልማት ስራ መግባታቸውንና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ነው የተመለከተው።


ዶክተር ሎው እንዳሉት፤ በሀገር አቀፍ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተፈጠረው የኑሮ ውድነት የግብርና ምርቶች ዋጋ መናር ባለሃብቶች በግብርና ልማት ላይ ለመሰማራት እንዲነሳሱ አድርጓል።


በጋምቤላ ወረዳ በግብርና ኢንቨስትመንት ከተሰማሩት ባሃለብቶች መካከል አቶ በኮች ማሞ በበኩላቸው፣ ዘንድሮ ከኮሚሽኑ የተሻለ ድጋፍ በማግኘታቸው በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ መግባቸውን ገልጸዋል።


ዘንድሮ በግብርናው ኢንቨስትመንት የተሻለ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብት ተወካይ አቶ እዮብ ገዛኸኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም