ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ለመቻል ያደረገችው ጥረት እንደ ምሳሌ የሚነሳ ነው

366

ሰኔ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችው ጥረት እንደ ምሳሌ የሚነሳ መሆኑን የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና ተናገሩ።


ፕሬዝዳንቱ በቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ለመቻል እያደረገች ያለችው ጥረት እንደ ምሳሌ የሚነሳ ነው።


የአፍሪካ አገራት ምግብ ለማምረት ድጋፍ ቢደረግላቸው እራሳቸውን ከመቻል አልፈው ወደ ሌሎች አገራት መላክ እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡


ኢትጵያን እንደ ምሳሌ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት በ 675 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ምርት ማምረትና ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የስንዴ ምርት ሰማንያ በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።


"ሀገሪቱ በዚህ አመት ምንም አይነት የስንዴ እህል ከውጭ አታስገባም በመጪው አመት ደግሞ ያለ ምንም እርዳታ የስንዴ ምርት ዋና ላኪ አገር በመሆን ወደ ውጭ መላክ ትጀምራለች" ብለዋል፡፡


በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 2 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ወደ ኬኒያ እና ጁቡቲ መላክ እንድትችል እየሰራች መሆኑንም አክለዋል።


አፍሪካ በግብርናው ዘርፍ የራሷን ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት ለማስቀረት እንዲሁም እራሷን ለመመገብ እንድትችል አገራት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡


በራሺያ እና ዩክሬን መካከል እተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት ወደ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን አፍሪካውያን ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል ብለዋል፡፡


አፍሪካ በመሬቶቿ ላይ ምርትን ማምረት ትፈልጋለች ያሉት ፕሬዝዳንቱ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ለአርሶ አደሮቿ ተደራሽ መሆን እንዳለባቸው አስታውቀዋል፡፡


የአፍሪካ ልማት ባንክ በራሽያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ የሚገኘው ጦርነት በአፍሪካ የምግብ ደህንት ላይ ያስከተለውን ተፅእኖ ለመቋቋም በግንቦት ወር 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር አፅድቋል፡፡


ድጋፉ በአፍሪካ የሚገኙ 20 ሚሊዮን አርሶ አደሮች 38 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እህል ለማምረት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡


ከዚህም ውስጥ ወደ 12 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ፣ 18 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በቆሎ፣ ስድስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሩዝ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን አኩሪ አተር እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡


ተጋላጭ አገራትን ለማገዝ ብድር ማቅረብ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገራት የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲገዙ እንዲሁም የአፍሪካን ግብርና ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማዘመን ተጨማሪ ብድር መቅረብ አለበት ብለዋል፡፡


የተሻለ ቴክኖሎጂ ለአፍሪካ ግብርና (ቲኤኤቲ) በተሰኘው የባንኩ ፕሮግራም ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ የሰብል አይነቶችን በአፍሪካ ለሚገኙ 12 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ማድረስ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም