በ10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የዕጣንና ሙጫ ምርት ከ600 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

199

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የዕጣንና ሙጫ ምርት ከ600 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ግብዓቶችን፣ የእርሻ መሳሪያዎችን እና የተቀናጀ ሜካናይዜሽን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡  

በተጨማሪም የደን ውጤቶች የሆኑትን ዕጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበክድ ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ገበያ በማቅረብ አገሪቷ ከዘርፉ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ እያደረገ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ እነዚህን የደን ውጤት ምርቶች በራሱ የማምረቻ ቦታ እና በዘርፉ ከተሰማሩ ማህበራትና ግለሰቦች ግዢ በመፈጸም 90 በመቶ የሚሆነውን ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡  

የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙኒኬሽንና ማህበራዊ ጉዳዮች አገልግሎት ሃላፊ ጋሻው አይችሉህም፤ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት አስር ወራት 2 ሺህ 300 ኩንታል ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ምርቶቹ በዋነኛነት የተላኩት ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ እና ላቲን አሜሪካ እንዲሁም ወደ አፍሪካ አገራት መሆኑን ጠቅሰው በ10 ወራት ለውጭ ገበያ ከቀረበ የዕጣንና ሙጫ ምርት ከ600 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል።

አሁን ላይ 400 ሺህ ዶላር የሚያወጡ የደን ውጤቶችን ወደ ውጭ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።   

የደን ውጤቶች በሚፈለገው ልክ ወደ ውጭ አገራት ለመላክ ህገ-ወጥ ንግድ ፈተና መሆኑን ጠቁመው ችግሩን ለማስቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

የአመራረት ዘዴውን ከአሁኑ በተሸለ መልኩ በቴክኖሎጂ የታገዘና ምርቱ ላይ እሴት በመጨመር ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለውጭ ገበያ ከቀረበው ዕጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤ እና አበክድ ምርት ከ13 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ታውቋል።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአገር ውስጥ ገበያ ከቀረበው ምርትም 79 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።