ሩስያ በስዊፍት ምትክ ያዘጋጀችው የገንዘብ መላኪያ ስርዓት ለብሪክስ ሀገራት ዝግጁ መሆኑን ገለጸች

189

ሰኔ 18 ቀን 2014(ኢዜአ) ሩስያ በስዊፍት ምትክ ያዘጋጀችው አዲሱ የገንዘብ መላኪያ ስርዓት (System for Transfer of Financial Messages (SPFS) ለብሪክስ ሀገራት ዝግጁ መሆኑን የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ገለጹ፡፡

በብራዚል፣ በህንድ፣ በቻይና እና በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ የገንዘብ ተቋማት ከአዲሱ የገንዘብ መልዕክት መላኪያ ስርዓት ጋር መገናኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚደንቱ አክለውም የብሪክስ ሀገራት ባንኮች ያለምንም ችግር ሩስያ በስዊፍት ምትክ ያበለጸገችውን አዲሱን የገንዘብ መልዕክት መላኪያ ስርዓት መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

ሩስያ ያበለጸገችው አዲሱ የገንዘብ መልዕክት መላኪያ ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ክፍያ ለመፈጸም አስተማማኝ መሆኑን በብሪክስ ቢዝነስ ፎረም ላይ የተሳተፉት ብራዚል፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚደንት ፑቲን የብሪክስ መገበያያ በሆነ ገንዘብ ዓለም አቀፍ ግምጃ ቤት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ የሩስያ የገንዘብ መልዕክት መገበያያ ስርዓት በገንዘብ ተቋማት መካከል ገንዘብ ነክ የመልዕክት ልውውጥ ስዊፍት የሚሰጠውን አቻ አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

ሩስያ ይህን አዲስ የገንዘብ ዝውውር መልዕክት መለዋወጫ ስርዓት መፍጠር የተገደደችው ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ምክንያት በምዕራባውያን የተሰነዘረባትን ማዕቀብ ለመቋቋም እንደሆነም ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም