የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የማህበራዊ ትስስር ቴክኖሎጂዎች በልጽገው ወደ ስራ ገብተዋል

104

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፤ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት በቴክኖሎጂ ባለቤትነት ለማረጋገጥ አዳዲስ አገር በቀል የማህበራዊ ትስስር ቴክኖሎጂዎችን አበልፅጎ ወደ ስራ ማስገባቱን ገለጸ።

ቴክኖሎጂዎቹ ጂሜይልን፣ ያሁን፣ ሆትሜይልን፣ ቴሌግራምን፣ ዋትስአፕንና ዙም ሚቲንግን ሊተኩ የሚችሉ ናቸው ብሏል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፤ የኢትዮጵያን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የቴክኖሎጂ ጦረኞችን በማሰለፍ የመመከት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም አስተዳደሩ አስታውቋል።

በዚህም ባለፉት 11 ወራት ብቻ የተሞከሩ 6 ሺህ ከሚጠጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ከ97 በመቶ የሚሆነውን በማክሸፍ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ሀብት ከኪሳራ ማዳኑን ጠቅሷል።

የአስተዳደሩ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት ኢትዮጵያን የሚመጥን ቁመና እንዲኖራቸው መሰራቱን አስታውሰዋል።

ከ15 ዓመት በፊት የተመሰረተው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም ከለውጡ ወዲህ  ራሱን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአሰራር በማዘመን ኢትዮጵያን የሚመጥን ደረጃ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም  አንዳንድ የውጭ ኃይሎችና የማህበራዊ የትስስር ገፅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሳይበር ጫና ሲያደርሱ እንደነበር ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የቴክኖሎጂ ባለቤትነት መረጋገጥ አለብን የሚል ጠንካራ መርህ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የመልዕክት ልውውጥና የማህበራዊ ተግባቦት ስራዎችን የሚያቀላጠፉ ኢትዮጵያ ሠራሽና ሀገር በቀል ስያሜ ያላቸው ቴክኖሎጂዎችን ማበልጸጉን ገልጸዋል።

ለአብነትም በተለያዩ የሀገሪቱ ቋንቋዎች መልዕክት የሚል ትርጉም ያለው "ኤርጋ" የተሰኘ ጂሜይልን፣ ያሁን፣ ሆትሜይልና ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መልዕክት መላኪያዎችን የሚተካ ቴክኖሎጂ መሰራቱን በመጥቀስ።

ቴክኖሎጂውን በመጠቀም በመረጃ ልውውጥ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን መከላከል መቻሉንም ጠቅሰዋል።

ሌላኛው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ ዙም ሚቲንግና ሌሎች የቪዲዮ ኮንፍረንስ ለመስጠት የሚያገለግሉ የውጭ ቴክኖሎጂዎችን የሚተካው "ደቦ" የተሰኘው  ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረው ቴክኖሎጂው በተለይ በፀጥታና ደህንነት ተቋማት ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገውኛ ሚስጥር የሚል ትርጉም ያለው "ሲርኩኒ" የተሰኘው ቴክኖሎጂ ደግሞ እንደ ዋተስአፕና ቴሌግራም ያሉ ሚስጥራዊ የመልዕክት መለዋወጫና የማህብራዊ ትስስር ገፅ በአስተዳደሩ ለምቶ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ደቦና ሲርኩኒ የተሰኙ ቴክኖሎጂዎች በርካታ ውጤት ማምጣታቸውን ጠቅሰው በቀጣይ ወደ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ለማስፋፋትና ቀስ በቀስም የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ በሀገር ደረጃ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይሰራል ነው ያሉት።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የሀገሪቱ ተቋማት ሀገር በቀል ዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲኖራቸው እየሰራ ሲሆን እስካሁንም ከ100 በላይ መተግበሪያዎችን በማልማት ለተቋማቱ ስራ ላይ ማዋሉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም