የበለፀገችና ደህንነቷ የተጠበቀ ሀገር ለመገንባት መላው ህዝብ ለሰላም ዘብ ሊቆም ይግባል--ዶክተር ሙላቱ ተሾመ

120

ጎንደር፤ ሰኔ18/2014  (ኢዜአ) "የበለፀገችና ደህንነቷ አስተማማኝ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት ህዝቡ በየአካባቢው ለሰላም ዘብ መቆም ይኖርበታል" ሲሉ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጥሪ አቀረቡ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው ሀገር የገጠማትን ወቅታዊ ችግሮች ከመፍታት ጎን ለጎን የችግኝ ተከላ መርሀግብሩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

ዶከተር ሙላቱ ተሾመ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት በሃገራችን በየዓመቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ችግኝ መትከል ባህል ሆኖ በመሰራቱ ለውጥ እየመጣ ነው።

ኢትዮጵዊያን የተራቆተ መሬትን መልሶ ደን ለማልበስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከዓመት ዓመት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል።

ሀገርን መልሶ የደን ባለጸጋ ለማድረግ የችግኝ ተከላ ስራው እንደ አገራዊ ግዳጅ ተወስዶ ከሌሎች የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቅሰው ሁሉም ሰላምን መጠበቅ እንዳለበት አስታውቀዋል።

ዶክተር ሙላቱ እንዳሉት የችግኝ ተከላውም ሆነ ሌሎች የልማት ሥራዎች በዘላቂነት እንዲከናወኑ በኢትዮጵያ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ይገባል።

ሰላምና ልማት ሁሌም እንደማይነጣጠሉ ጠቁመው፤ "ለዘላቂ ሰላም ሁላችንም ተግተን ልንሰራ ይገባል" ሲሉ ገልፀዋል።

‘’ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላምን ይንከባከብ፤ ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍንም የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ያድርግ’’ ይህ ሲሆን ሰላሟ የተረጋገጠና ደህንነቷ የተጠበቀ ሀገር ትኖረናለች" ብለዋል።

ደህንነቷ የተጠበቀና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ህዝቡ በየአካባቢው ለሰላም መረጋገጥ ተግቶ መስራት እንደሚገባው ዶክተር ሙላቱ አስገንዝበዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ መትከል የህልውና ጉዳይ መሆኑን በአግባቡ ተገንዝቦ ሁሉም እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።  

የተተከሉ ችግኞች ለውጤት እንዲበቁ በየደረጃው ጠንካራ አደረጃጀት በመፍጠርና ልምዶችን በመቀመር ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ለቀጣይ ትውልድ ለኑሮ ምቹ የሆነችና የበለጸገኝ ሀገር ለማስረከብ በአሁኑ ወቅት የሚሰሩ ሥራዎች ወሳኝ መሆናቸውን አቶ ኃይለማርያም ጠቁመው "የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለውጤት ማብቃት ይገባል" ብለዋል።

"በሀገራችን ከሰላም ጋር በተያየዘ ያጋጠሙ ችግሮችን በሰከነና በተረጋጋ መንገድ መፍትሄ በማበጀት ዘላቂ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሰሞኑን በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን የጭካኔ ድርጊት ያወገዙት አቶ ሃይለማርያም፣ መሰል የጥፋት ተግባራት እንዳይፈጸሙ ተባብሮ መስራትና አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግበር ለሚተከሉት የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ማስጀመሪያ መርሀግብር ትናንት በጎንደር ከተማ አዘዞ ቀበሌ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም