የኢትዮጵያ አየር ኃይል በስልጠና እና አቬዬሽን ቴክኖሎጂ ትጥቁን እያዘመነና አቅሙን እያሳደገ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

137

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በስልጠና እና አቬሽን ቴክኖሎጂ ትጥቁን እያዘመነና አቅሙን እያሳደገ መምጣቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተዋጊ አውሮፕላንን ጨምሮ በተለያዩ አውሮፕላን አብራሪነት የሰለጠኑ አባላቱን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በአፍሪካ ስመ ጥር የነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከደርግ ውድቀት በኋላ የማፍረስ አባዜ በተጠናወታቸው ኃይሎች ለ30 ዓመታት “ዳዋ” ለብሶ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ግን ኢትዮጵያን የሚመጥንና እንደ ቀድሞ ዝናው በአፍሪካ ስመጥር አየር ኃይል የመገንባት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በስልጠና እና አቬሽን ቴክኖሎጂ ትጥቁን እያዘመነና አቅሙን እያሳደገ መምጣቱንም ተናግረዋል።

አዲስ ትጥቅ በመግዛት፣ የነበረውን በማደስ በአጠቃላይ ነባር አቅሙን በማደስ በአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ጦርነትን ከሩቅ የሚያስቀር ኃይል ለመገንባት ተግተን እንሰራለን ያሉት ፌልድ ማርሻሉ፤ በመሰረተ ልማና በሰው ኃይል ልማት አስደናቂ ለውጦች መታየታቸውን ተናግረዋል።

የአየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ረጅም ታሪክ ያለው አየር ኃይል የአገር ሉዓላዊነትን በማስከበር ተልዕኮ አይተኬ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሰራዊቱ ከብሔርተኝነትና መንደርተኝነት ወጥቶ በአገራዊ አስተሳስብ በመመራት ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋሙንም አስረድተዋል።

የአንድን ብሔር፣ ሐይማኖት፣ ማንነት እና የፖለቲካ አስተሳስብ መወገን በሰራዊቱ ክልክል ሆኖ በመገንባቱ ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።

በዚህም ተቋሙ በስልጠና ችእና አቬሽን ቴክኖሎጂ ትጥቅ በማዘመንና አቅሙን በማሳደግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአገር የማዳን ዘመቻዎች ወቅት በታጠቀው ዘመናዊ ትጥቅ ወገንን ያኮሩና ጠላትን ድባቅ የመቱ ተልዕኮዎችን መፈጸሙን ገልፀዋል።

ለሰራዊቱ ምቹ የስራ ከባቢ በመፍጠር አየር ሃይሉን የመገንባት እና ይበልጥ የማጠናከር ስራችንን እንቀጥላለን ሲሉም አረጋግጠዋል።