የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለአነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞቹና አቅመ ደካሞች የበዓል ስጦታ አበረከተ

1088

አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ለአነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞችና ለአቅመ ደካማ የአካባቢው ነዋሪዎች የበዓል ስጦታ አበረከተ።

ድርጅቱ የዘንድሮውን አዲስ አመት በጎ ለማድረግ በማሳብ ከተቋሙ በተሰጠና ከሰራተኞች በተሰበሰበ ገንዘብ ነው ድጋፉን ያደረገው።

በዚህም መሰረት ተቋሙ ለ57 ዝቀተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሰራተኞች አራት በሬ በማረድ በቅርጫ አከፋፍሏል።

በተጨማሪም ከተቋሙ ውጪ ለሆኑ የአራዳ ክፍል ከተማ ወረዳ 9 አቅመ ደካሞች የበግ፣ ዶሮ፣ እንቁላልና የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ ለልጆቻቸውም የመማሪያ ቁሳቁስ አበርክቷል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት ታደሰ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስት “የአዲስ አመት ስጦታ ለእናት አገሬ” በሚል መርህ በዚህ አመት ተከታታይነት ያለው የበጎ ተግባር ስራ ተሳታፊ በመሆን የፕሬስ ድርጅትም የአዲስ አመት ስጦታ መርሃ-ግብር አከናውኗል።

“ይህን መሰል ድጋፍ መደረጉ በተቋሙ ውስጥ ያሉትን ሰራተኞች የስራ ተነሳሽነት ከመጨመር አልፎ እርስ በርስ ያለውን መስተጋብር ያጠናክራል” ሲሉም አክለዋል።

የዚህ ዓይነቱ የመተሳሰብ መንፈስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የተናገሩት ዋና ስራ አስኪያጁ ድርጅቱ ወደፊት የሰራተኞችን ደመወዝ ለማሻሻልና ነዋሪውን ደግሞ ለማቋቋም በሚችለው መጠን እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ድጋፉ ከበዓል አልፎ ዘላቂ ቢሆን የተጀመረውን የመደመር ስሜት በማጠናከር ለአገር አንድነት የሚኖረው ፋይዳም የላቀ እንደሆነ ተጠቁሟል።

ድጋፍ የተደረገላቸው እነዚሁ አካላት ደስታቸው የላቀ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ድጋፉና መተሳሰቡ ሊቀጥል የሚገባው እነደሆነ ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  ከመንግስታዊዎቹ የሚዲያ ተቋማት መካከል ሲሆን አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ በሪሳና አል-አለም ጋዜጦችን ጨምሮ የተለያዩ ዜናና ዜና ነክ መረጃዎችን በተለያዩ ህትመቶች የሚያሰራጭ የመገናኛ አውታር ነው።