በግብርናው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን ተስፋ የሰጡ ናቸው- የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት

100

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) የበጋ ስንዴ ልማትን ጨምሮ በግብርናው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶች ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን ተስፋ የሰጡ መሆናቸውን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት ተናገሩ፡፡

በግብርናው መስክ የተመዘገቡ ስኬቶችን በሌሎች ዘርፎች ላይ በመድገም የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እንደሚሰራም ነው ያነሱት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጎ የወደፊት አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡

በዚህም በተለይ በግብርናው መስክ የተመዘገበውን ስኬት ይበልጥ በማጠናከርና ወደ ሌሎች ዘርፎች በማስፋት ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል አሻድሊ ሀሰን፤ እንደ ሀገር የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኩታ ገጠም እርሻን ከማስፋፋት ባሻገር አርሶ አደሮች ዘመናዊ ትራክተሮችን ተጠቅመው እንዲለሙ ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የእርሻ ትራክተሮችን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብአቶችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ኢትዮጵያን ከስንዴ ተመፅዋችነት ወደ ውጭ ላኪነት ለማሸጋገር የሚያስችል ውጤታማ ጉዞ ጀምረናል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮችን ከባንክ ጋር ቀጥታ በማገናኘት ብድር የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት ገበያ መር የግብርና ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ላይ ብቻ የመጣ እዳ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው መሆኑን ገልጸው ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በኢትዮጵያ ያለው የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም የኑሮ ውድነቱንና የዋጋ ንረቱን ለመቆጣጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አቅርቦቱን መጨመርና የስራ እድል በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትርና የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባል ሙፈሪያት ካሚል፤ ኢትዮጵያ በአንበጣ መንጋ፣ በጎርፍና ሌሎች ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች እየተናጠች ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ሳይቋረጥ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ አገርን የሚታደጉ ብሎም ለአፍሪካ አህጉር የሚተርፉ አዳዲስ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አሁንም የኢትዮጵያ ፈተናዎች እንደሆኑ ናቸው የሚሉት ስራ አስፈፃሚዋ፤ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ጉዞ ለአፍታም ቢሆን አይቆምም ብለዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግስት ህዝቡን በማስተባበር አሰራሮችን ማሻሻልና ምርታማነትን ማሳደግ የሚችልበት አካሄድ ገቢራዊ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡