የወይጦ-ቱርሚ የ120 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው- የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ

115

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የወይጦ-ቱርሚ የ120 ኪ.ሜ አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ገለጹ።

ግንባታው ከተጀመረ ሰባት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን እስካሁን በተያዘው ዓመት ለመስራት ከታቀደው በላይ መከናወኑ ተገልጿል።

በመንግስት ሙሉ ወጪ እየተገነባ ያለው መንገድ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ ሲሆን በተያዘለት እቅድ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጠናቀቅም በዋናነት የወይጦ፣ አልቦሬ እና ቱርሚ ከተሞችን የሚያገናኝ ሲሆን የጉዞ ሰዓትን የሚያሳጥር መሆኑም ታውቋል።

የመንገዱን ግንባታ እያከናወነ ያለው የራማ ኮንስትራክሽን የወይጦ ቱርሚ መንገድ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ኤርሚያስ መኮንን፤ መንገዱን ገንብቶ ለማጠናቀቅ በአራት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በአራት ዓመታት ለማጠናቀቅ እቅድ የተያዘለት ቢሆንም በአሁኑ የግንባታ ፍጥነት ከቀጠለ ከተያዘለት ጊዜ ቀደም ብሎ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ገምተዋል።

የሲሚንቶ እጥረት፣ የወሰን ማስከበርና ከካሳ ክፍያ ጋር የተያያዙ ችግሮች ደግሞ በቀጣይ ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

በመንገድ ግንባታ ሂደቱ የመሬት መሸርሸር አደጋን ለመከላከል በዩኔስኮ የተመዘገበው የኮንሶ ብሄረሰብ የእርከን ስራ ቴክኖሎጂ ገቢራዊ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ አማካሪ መሀንዲስ ተጠሪ ኢንጅነር ገዛሀኝ አሰፋ፣ የመንገድ ፕሮጀክቱ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

መንገዱ በተባለው ጊዜ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከመፍታት አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በፕሮጀክቱ ክልል ስር የሚገኙ አነስተኛ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማነት የሚያድጉበትን ምቹ እድል ሚፈጠር መሆኑም ተገልጿል።

በተጨማሪም ሥፍራው የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ፣ የኦሞ ሸለቆ አርኪኦሎጂካል ሳይት እንዲሁም በዞኑ የሚገኙ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ እና ቁሳዊ የቱሪስት መስህቦች (በተለይም የሐመር ብሔረሰብ) መዳረሻ እንደመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

የኦሞ ወንዝን ተከትለው በሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች የሚመረቱ የተለያዩ የፍራፍሬ ምርቶችን ወደ ማዕከላዊ ገበያ በፍጥነት በማድረስ በኩልም ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

አሁን ላይ መንገዱ ካለው ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንፃር በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ እየተገነባ ሲሆን በገጠር 10 ሜትር እንዲሁም በከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር የጎን ስፋት ይኖረዋል፡፡