የአሸባሪዎችን እኩይ ሴራ በማምከን የአረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

82

ጋምቤላ ፤ ሰኔ 18/2014 (ኢዜአ) የአሸባሪዎችን እኩይ ሴራ በማምከን በክልሉ የአረንጓዴ አሻራና ሌላውንም የግብርና ልማት ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ለአራተኛው ዙር የአረንጓዴ አሸራ ልማት መረሃ ግብር ከ9 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለተከላ መዘጋጀቱ ተመልክቷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቅርቡ አሸባሪው ሸኔና እራሱን  “ጋነግ” ብሎ የሚጠራው ቡድን በጋምቤላ ከተማ ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክሩም ጸጥታ ኃይሎች ከህዝቡ ጋር ተቀናጅተው በወሰዱት እርምጃ አካባቢውን ወደ ቀድሞው ሰላምና የልማት እንቅስቃሴ መመለስ ተችሏል።

የአሸባሪዎቹን እኩይ ሴራ በማምከን በክልሉ ልማትን ለማፋጠን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ቢሮው በክረምቱ ያቀዳቸውን የአረንጓዴ አሻራና የመኸር ግብርና ልማት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አቶ አጃክ ገልጸዋል።  

በክልሉ በዘንድሮው አራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ልማት ከ9 ነጠብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች መካከልም 65 ከመቶ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የፍራፍሬ ችግኞች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

በተያዘው የመኸር ወቅት ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የምግብ ሰብል  ለማልማት የንቅናቄ ስራ መካሄዱን ያመላከቱት ሃላፊው፤ ከዚህም ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።

የክልሉ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጃክ ጁዎሴፍ በበኩላቸው፤አሸባሪው ሸኔና እራሱን ጋነግ ብሎ የሚጠራው ቡድን የክልሉን ሰላም ለማወክ የጠነሰሱት ሴራ በጸጥታ ሃይሉ በማምከን አከባቢው ወደነበረበ ሰላምና ልማት መመለሱን ተናግረዋል።

በቢሮው የያዘውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት እቅድ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ ክልሉ ወደ ቀድሞው ሰላሙ በመመለሱ የአረንጓዴ አሻራና የመኸር የግብርና ልማትን ታቅዶ  ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ባለሙያ አቶ ኬት ቾል ናቸው።