ከሳዑዲ አረቢያ እስካሁን ድረስ ከ40ሺህ በላይ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ተመልሰዋል

92

ሰኔ 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከሳዑዲ አረቢያ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ እስካሁን ድረስ ከ40ሺህ በላይ ዜጎችን መመለስ መቻሉን ይፋ አደረገ።

16 የመንግስት መስሪያቤቶችን ያካተተው ብሔራዊ ኮሚቴ ባለፉት ወራት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

ስብሰባውን የመሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ሲራጅ ረሽድ እንደተናገሩት እስካሁን 111 ጊዜ በተደረጉ በረራዎች 40,794 ዜጎችን ወደ ሀገራቸው መመለስ ተችሏል።

አምባሳደሩ 102 ሺህ ዜጎችን ለማስመለስ ከተያዘው ዕቅድ አንጻር እስከ አውሮፓውያኑ ሰኔ 22 ድረስ ማሳካት የተቻለው 40 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቀጣይም ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም በተቻለ ቅንጅታዊ አሰራር የታቀደውን ግብ ለማሳካት በትብብር መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተነስቷል።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንም ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ራሱን በቻለ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑ በውይይቱ ተጠቅሷል።

በውይይቱ ላይ በብሔራዊ ኮሚቴው የተካተቱ ተቋማት ተወካዮች መሳተፋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም