የተለያዩ ጥቃቶችን በማድረስ ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ ይቀጥላል- የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ

ሰኔ 16/2014/ ኢዜአ/ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በደረሱ ጥቃቶች ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የማድረግ ስራ በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሰሞኑን ባስተላለፉት መልዕክት “ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የምንሰጠው ተግባራችን ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ጸጋ፤ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በማንነት ሽፋንና በተለያየ መልኩ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ተሳትፎ በሚያደርጉ አካላት ላይ እየተወሰደ ስላለው እርምጃና ሙስናን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በንጹሃን ወገኖች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት አውግዘው፤ በወንጀሉ ፈፃሚዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ የመውሰድና ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ሃይማኖትንና ማንነትን ሽፋን በማድረግ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደረሰ ጥቃት ተሳትፎ የነበራቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር በማዋል ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ምርመራ መቀጠሉንም ገልጸዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በንጹሃን ላይ በተፈፀመው ቃጠሎ በወንጀሉ ተሳትፎ አላቸው ተብለው በተጠረጠሩ የጸጥታ አካላት ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ወደ ሌላው ለመሄድ መጀመሪያ እራስን መገምገምና ማጥራት ቀዳሚ ስራ ሊሆን ይገባል በሚል የሙስና ተግባር ዝንባሌን ለመረዳት በተቋሙ ውስጥ ጥናት መደረጉን ተናግረዋል።

የተካሄደው ጥናት ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ ለአብነትም፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሽ ያለሆኑ 29 ግለሰቦች ላይ ከ65 ሚሊየን ብር በላይ ያለአግባብ በመንግስት ገንዘብ ላይ ምዝበራ እንዲፈጸም ባደረገ ግለሰብ ላይ ክስ መመስረቱንም ገልጸዋል።

ለተቋሙ በቀረቡ ጥቆማዎች መሰረት ሶስት የተቋሙ ሰራተኞች የሙስና ወንጀል ሲፈጽሙ ተገኝተው የክስና ምርመራ ተግባር እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው አመላክተዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በሀይማኖትና በማንነት ሽፋን ተደርገው የተለያየ አጀንዳ ባላቸው የጥፋት አቀናባሪዎች በተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ አብዛኞቹ እልባት እየተሰጣቸው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም