አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶና አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር የሹመት ደብዳቤያቸውን አቀረቡ

2267

አዲስ አበባ መስከረም 1/2011 በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላካው መግለጫ እንዳስታወቀው  በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ የሹመት ደብዳቤያቸውን ሲያቀርቡ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ጠንካራና ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት በአምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ የስራ ቆይታ ይበልጥ እንደሚጠናከርም እምነታቸውን ገልፀዋል።

አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ወዳጅነትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ታሪካዊ መሆኑንና ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መኖሩን ገልፀው ፈጣን የኢኮኖሚ  እድገት ለማስመዘገብና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ለመሥራት ጊዜው አመቺ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በአልጀሪያ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አሚን አብዱልቃድር ለአልጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብድልቃድር መሳሂል የሹመት ደብዳቤያቸውን በትናንትናው እለት አቅርበዋል።

አምባሳደር አሚን በአገራችን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ እየተወሰዱ ስላሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች እንዲሁም አገራችን ለቀጠናው ሰላምና ጸጥታ እየተጫወተች ስላለው ገንቢ ሚና ገለጻ አድርገዋል።

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለተደረሰው የሰላም ስምምነት የአልጀርሱ ስምምነት ትልቅ መሰረት ሆኖ ማገልገሉን ገልጸው በጅቡቲና ኤርትራ መካከል የነበረውን ቅራኔ ለመፍታት መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያና ከሱማሊያ ጋር በመሆን ያላሰለሰ ጥረት ማድረጓን አክለዋል።

የአልጀሪያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብድልቃድር መሳሂል በበኩላቸው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተጀመረውን የሰላም ሂደት የአልጄሪያ መንግስት እንደሚደግፍ ገልጸዋል።

የሰላም ስምምነቱ ለመላው የአፍሪካና ዓለም አገሮች ሞዴል መሆን የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና በአልጀሪያ መካከል ያለው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ጠንካራ መሆኑንም ገልጸው ይህንንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንግስታቸው ጠንክሮ እንደሚሰራ ማስታወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አመልክቷል።