የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለመቄዶንያ አስፈላጊውን እገዛ ታደርጋለች- ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

158

ሰኔ 17 ቀን 2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል አስፈላጊውን እገዛ የምታደርግ መሆኑን ፓትያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ፡፡

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ሊቀነ ጳጳሳት፣ የቤተክርስትያኗ የየመምሪያው ኃላፊዎችና የአብያተ-ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች የመቄዶንያ አረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከልን ጎብኝተዋል።

በማዕከሉ የሚከናወኑ የበጎ አድራጎትና የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት 40 አቅመ- ደካሞችን በማሰባሰብ ሥራ ጀምሮ በአሁኑ ወቅት ከ7 ሺህ በላይ ሰዎችን እየደገፈ መሆኑ ተገልጾላቸዋል፡፡

በማዕከሉ የሚከናወነው ተግባር ትልቅ ዋጋ ያለውና የሚያስመሰግን በመሆኑ ሕብረተሰቡ ለዚህ መልካም ተግባር ድጋፍ እንዲያደርግ ፓትሪያርኩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቤተክርስቲያኗ በተቋሙ ለሚሰሩ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠው፤ ሰባኪያን ወንጌል በሚያስተምሩበት አውደ-ምህረት ማዕከሉን እንዲያስታውሱ፣ መገናኛ ብዙኃንም ማዕከሉን በማስተዋወቅ ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የማዕከሉ መሥራች ብንያም በለጠ፤ ማዕከሉ አረጋውያንን እና የአዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ክረምቱን ተከትሎ በርካታ አረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን ወደ ማዕከሉ እየገቡ ሲሆን በቀጣይም ከ20 ሺህ በላይ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ከጎዳና የማንሳት ዕቅድ አለን ብለዋል።

ማዕከሉ በ2 ቢሊየን ብር እያስገነባው ያለው ህንጻ 65 በመቶ መድረሱንና ተጨማሪ በ6 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ህንጻ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንገኛለንም ነው ያሉት ።

ሕብረተሰቡ ለማዕከሉ እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም